በመርካቶ የ32 ቀበሌ ነዋሪዎች “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለእስር አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ፖሊስን ተቃወመ

በመርካቶ የ32 ቀበሌ ነዋሪዎች “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለእስር አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ፖሊስን ተቃወመ

 ቅዳሜ ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፖሊስ በሰፈሩ ተሰማርቶ ነበር
/
በተለምዶ 32 ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው የመርካቶ አካባቢ /ፋሲል ፋርማሲ አካባቢ/ ያሉ ነዋሪዎች፣ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 3/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ፣ “ተጨማሪ ልጆቻችንን ለፖሊስ አሳልፈን አንሰጥም”በማለት ከፖሊስ አባላት ጋር ግብግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከሰፈሩ በርካታ ወጣቶች ሰሞኑን ታስረዋል።

ቅዳሜ ከሰዓት አንድ ተጨማሪ ወጣት በመያዝ ወደ ሰፈሩ የገባው የፖሊስ ኃይል፣ ሲቪል ለብሶ የነበረ ሲሆን፣ ወጣቱን ለመያዝ ሲሞክር ነዋሪው ጣልቃ ገብቶ፣ “ወጣቱን አሳልፈን አንሰጥም” በማለታቸው ግብግብ ተፈጥሮ፣ በጊዜው የነበሩት 4 ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች ሽጉጥ አውጥተው ምንም መሳሪያ ያልያዘውን ነዋሪ እያስፈራሩ ልጁን ይዘው ከአካባቢው ወጥተዋል፡፡ ፖሊሶቹ መሳሪያ ሲያወጡ የአካባቢው ሽማግሌዎች ነገሮችን ለማብረድ ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ፣ ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር በቦታው የነበሩት ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሰ በኋላ ድብደባ የደረሰበት ሲሆን፣ ወደተያዘበት አና ተቃውሞ ወደተነሳበት አካባቢ በርካታ ክላሽ የታጠቀ ፖሊስ ተልኮ አካባቢው ላይ ከፍተኛ ውጥረት ሰፍኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ ተጨማሪ ወጣቶች ከሰፈሩ እየለቀቁ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተገደዋል፡፡ ቅዳሜ ዕለት በፖሊስ በኩል የነበረው ፍላጎት ከአንድ በላይ ወጣት ለመያዝ እንደነበር እና ነዋሪው ባስነሳው ተቃውሞ እንደከሸፈ በበሰፈር ውስጥ እየተነገረ ይገኛል፡፡

Source – Balderas party