በዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ለተጎዳ የአፍሪካ ሀገራት 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደረግ ነው

May be an image of 1 personየዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ለተጎዱ የአፍሪካ ሀገራት 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተገለፀ፡፡

ቀደም ሲል በኮቪድ -19 ከተፈጠረው የኢኮኖሚ ድቀት ለማገገም የሚታገለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዩክሬን ጦርነት ሌላ ጫና ላይ መውደቁ የአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ከአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ዳይሬክተርዋ ከአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ ከማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮች ጋር በዩክሬን ያለውን ቀውስ ሊያደርስ ስለሚችለው ተፅእኖ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱም በጦርነቱ ምክንያት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የምግብ ዋጋ መናር፣ የዕዳ አገልግሎት ግዴታዎች እንዲሁም ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ማጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

ከአፍሪካ አገራት 12 የሚሆኑት ብቻ የተጣራ ኢነርጂ ላኪዎች ሲሆኑ ቀሪዎች 42ቱ አገራት ደግሞ ኢነርጂ አስመጪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው “ያላቸው የበጀት ቦታ ውስን በመሆኑ ይህ በጣም አስደንጋጭ ነው” ይላሉ።

“በርካታ የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለመቻላቸውን አንስተው ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉት ተጠቃሽ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡

ከሩሲያ እና ዩክሬን የሚመጡ የስንዴ ምርት ተያይዞ በአንዳንድ ሀገሮች ላይ ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ንረት መስተዋሉንም ጠቁመዋል፡፡

ከስቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ቫንዲል ሲህሎቦ ባደረገው ትንተና “የአፍሪካ አገሮች በ2020 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ከሩሲያ ማስገባታቸው አንስቷል፡፡

“ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ስንዴ ሲሆን 6 በመቶ ደግሞ የሱፍ አበባ ዘይት እንደነበረ ጠቁሟል፡፡

ግብፅ ግማሽ የሚጠጋ ድርሻ የነበራት ሲሆን ሱዳን፣ ናይጄሪያ ታንዛኒያ፣ አልጄሪያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ድርሻ እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡

ውይይቱን ተከትሎ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች የመቋቋም አቅምን ከፍ ለማድረግ በዘላቂነት እንዲያገግሙ ለማበረታታት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።