ሕወሓት የጀመረው ዉጊያ በአፋር ክልል ዞን ሁለት በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች እንደቀጠለ ነዉ።

በአፋር ክልል የሚደረገዉ ጦርነት ሰላማዊ ሰዎችን መግደል፣ ማፈናቀሉና ሐብት ንብረት ማዉደሙን መቀጠሉን ተፈናቃዮችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አስታወቁ።በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ና በተለያዩ የአፋር ኃይላት መካከል የሚደረገዉ ዉጊያ አሁንም በአፋር ክልል ዞን ሁለት በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች እንደቀጠለ ነዉ።

ጀርመን ራዲዮ ያነጋገራቸዉ ተፋናቃዮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች ለተፈናቃዩ በቂ ርዳታ እያቀረቡ አይደለም።የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አደም ሙሳ በበኩላቸዉ በአፋር ክልል ለወራት እየተካሄደ ባለው ጦርነት የፌዴራል «መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ አልተወጣም።» በማለት ይወቅሳሉ። የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ሚንስትር ለገሰ ቱሉ በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግስት በአፋር የሚደረገዉን ዉጊያ ተቀምጦ የተመለከተ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች እገዛ ያደርጋል ብለው ነበር።

Äthiopien vom Krieg betroffene Binnenflüchtlinge aus Abala Afar-Region በአፋር ክልል የሚካሄደው ጦርነት በመቀጠሉ ዜጎች ከአከባቢው በየእለቱ  እየተፈናቀሉ፤ በጦርነቱም ብርቱ ዋጋን እየከፈሉ መሆኑን ተፈናቃዮች እገለጹ ነው፡፡ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የአፋር ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው በተለይም በአሁኑ ወቅት በአፋር ዞን 2 በሁለት ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ዜጎች ቤት አልባ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ በርሳቸው እምነት በአፋር ለወራት እየተካሄደ ባለው ጦርነት የፌዴራል መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትን በሚገባ አልተወጣም፡፡

ሰዓዳ ኢብራሂም በአፋር ክልል ዞን 2 የአባዓላ ከተማ ነዋሪ የነበረች ሲሆን ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ነበር አሁን በአከባቢው ተስፋፍቶ በሚገኘው ጦርነት ከእነ ቤተሰቦቿ በመፈናቀል በሌላኛዋ ከተማ ኢረብቲ የተጠለሉት፡፡ ይሁንና በህወሓት ኃይሎች ወዲያው የተስፋፋው ጦርነት ለአንድ ወር ያህል ከተሸሸጉባት ከተማም ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም ተፈናቅለው አስከፊ ያሉትን የ50 ኪ.ሜ. ገደማ የእግር ጉዞ ወደ አፍዴራ ይያያዙታል፡፡ እሷ እና ውስን ቤተሰቦቿ በአፍዴራ ከተጠለሉ ሳምንታት ቢቆጠሩም እስካሁን በመንገድና በአከባቢው የሚፈተኑ ሰዎች ቁጥር ግን ቀላል አይደለም ትላለች።

እንደ የአብዓላዋ ተፈናቃይ አስተያየት ከተለያዩ አምስት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአፍዴራ በየሰው በረንዳ እና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የመንግስት ቢሮዎች ደጃፍ ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ሌላው የኢሬብቲ ከተማ ተፈናቃይ መሃመድ ኑር ዑስማን አክለው እንደነገሩን አብዓላ፣ መጋሌ፣ ኢረብቲ እንዲሁም አሁን ላይ ጦርነት እየተደረገበት ነው ያሉት በርሃሌ እና ኮኖባ ወረዳዎች ብርቱ የሰዎች መፈናቀል ገጥሟል።
የነዋሪዎቹን አስተያየት ደግመው ያረጋገጡት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት አሁን ላይ በተለይም በሁለት የአፋር ዞን 2 ወረዳዎች ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡

እንደ የአፋር ተፎካካሪ ፓርቲ ኃላፊው እምነት በአፋር ለወራት እየተካሄደ ባለው ጦርነት የፌዴራል መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትን በሚገባ አልተወጣም፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፌዴራል መንግስት በአፋር በኩል እንደ አዲስ የተስፋፋውን ጦርነት ተቀምጦ የተመለከተ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች እገዛን ያደርጋል ብለው ነበር፡፡ ህወሓት በበኩሉ በአፋር በኩል የትግራይ ህዝብ ህልውና ስጋት ሆኗል ያለውን የኤርትራ ሰራዊት ለመዋጋት ጦርነቱን መክፈቱን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም ግን በአፋር የህወሓት ኃይሎችን እየተዋጋ የሚገኘው የአፋር አርብቶ አደር እና የክልሉ ፀጥታ አካላት ብቻ ናቸው ሲሉ ሞግተዋል።