” ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት አልተሰጠውም ” – የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር

” ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት አልተሰጠውም ” – የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር

የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር የአፋር ክልል ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት አልተሰጠውም ሲል ወቅሷል።

ተፈናቃዮቹ ባሉበት አስከፊ ሁኔታ የሞት አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ገልጿል።

የማህበሩ አስተባባሪ የሆኑት ቫለሪን ብራውኒንግ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ፥ ” የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፍ ያንን ያህል ሰፊ ነው። በዚያ ላይ በተበታተነ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት ይህም ሌላ ፈተና ነው። ምግብ የለም ፣ ውሀ የለም ፣ አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ የሉም። የተፈናቀሉት ሰዎች በረሃብ በጥማት እና በበሽታ ምክንያት የሞት አሰጋ አንዣቦባቸዋል። ” ብለዋል።

ማህበሩ በግመል እና በሌላም አማራጭ ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሞያዎች ቡድን አሰማርቶ ተፈናቃዮችን ለመድረስ ጥረት አድርጎ የነበር ሲሆን መድረስ የቻለው ግን ጥቂቶችን ብቻ ነው። በርካቶች ወደ መጠለያ ጣቢያ ለመምጣት ስጋት አለባቸው።

ብራውኒንግ ፥ ” ረጅም ርቀት የሚወነጨፉ ታንኮች እና ከባድ መሳሪያዎች ባስከተሉት ጉዳትና ይሄን ተከትሎ በፈጠረባቸው ጭንቀት ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ለመምጣት ይፈራሉ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በጦርነቱ አጥተዋል። በዚህም በጣም ጭንቀት ውስጥ በመሆናቸው ወደ አስፓልት መንገዶች አይወጡም፤ አንድ ላይ መሆን አይፈልጉም፤ በሚችሉት ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ለአደጋ ሳይጋለጡ የሚቆዩባቸውን ተግባር ነው የሚሰሩት ” ብለዋል።

የአፋር የአርብቶ አደር ማህበር ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ለሬድዮ ጣቢያው ገልጿል።