ሕወሓት በአፋር ክልል ጦርነቱን አጠናክሮ በመቀጠል የኢትዮ ጂቡቲን መስመር ለመቆጣጠር እየተዋጋ ነው

የአፋር ክልል ባወጣው መግለጫ ጁንታው ሰርዶን ለመቆጣጠር እንደ አዲስ በኪልበቲ ረሱ ዞን የከፈተውን ከባድ ጦርነት አጠናክሮ ቀጥሏል! ብሏል

ክልሉ በመግለጫው እንደገለጸው ጁንታው ከታህሳስ 10/2014 ጀምሮ እንደ አዲስ በአፋር በኩል በከፈተው ጦርነት በኪልበቲ ረሱ ዞን የተለያዩ አምስት ወረዳዎችና አንድ ከተማ መስተዳድር ማለትም በአብአላ ከተማ አስተዳደር፣ በአብአላ ወረዳ፣ በመጋሌ ወረዳ፣ በኤረብቲ፣ በኮነባ እና በራህሌ ወረዳዎች በተደጋጋሚ ጦርነት በመክፈት ሰርዶን በመያዝ የኢትዮ ጂቡቲን መስመር ለመቆጣጠር እና አፋርን እንደ መደራደሪያ ለመጠቀም ካሁን በፊት ሚሌን ለመቆጣጠር ያደረገውን ትግል በጠነከረ መልኩ ውጊያ በማካሄድ በራህሌና ኮነባንም በቁጥጥሩ ስር አውሏል።
የአፋር አናብስቶች አሸባሪው ህወሀት ከተቆጣጠራቸው አብአላ ከተማ አስተዳድር፣ አብአላ ወረዳ ፣ መጋሌ ወረዳ እና ኤረብቲ ወረዳዎች እንዲሁም ከባድ ጦርነት ከከፈተባቸው በበራህሌ እና ኮነባ ተጨማሪ ማስፋፋት እንዳያደርግ ከባድ ፊልሚያ ቢያደርጉም ጁንታው ይዞት በመጣው ሜካናይዝድ ጦር በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በራህሌና ኮነባ ወረዳንም በመቆጣጠር የተለመደውን ጅምላ ግድያና ዘረፋ እያካሄደ ነው።
በኪልበቲ ረሱ ዞን በተለያዩ ቦታዎች ጁንታው ጦርነት በመክፈት ህዝብ ላይ በከባድ መሳሪያዎች በመተኮስ በአሰቃቂ ሁኔታ የመጨፍጨፍ እና የማሸበር ተግባሩን በመስራት ኪልበቲ ረሱ ዞንን በአጠቃላይ በመቆጣጠር ሰርዶ ድረስ ዘልቆ በመግባት የኢትዮ ጂቡቲ መተላለፊያ ኮሪደር ዋና መስመርን ለመቁረጥ ትልቅ ሜካናይዝድ የሆነ ውጊያ እያካሄደ ነው።
አሸባሪው ቡድን ከ ወር በላይ በሆነው በዚህ አዲስ በከፈተው ግንባር በተቆጣጠራቸው ወረዳዎችና ጦርነት እያካሄደባቸው ባሉ ወረዳዎች ከባድ የሆነ የሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራን አድርሷል። ንፁሀንን በጅምላ ጨፍጭፏል፣ የተለያዩ ተቋማትን ሌሎች ቦታዎች ሲያደርግ እንደመጣው ሁሉ ከባድ ዘረፋ እና ውድመት በመፈፀም ላይ ይገኛል፣ ከ 300 ሺህ በላይ ንፁሀን ዜጎችም ጁንታው በሚወረውረው ከባድ መሳሪያ እና ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በአፋር ኪልበቲ ረሱ ዞን ጁንታው እንደ አዲስ የከፈተው ጦርነት አሁንም አልቆመም፣ ቡድኑ ያለ የሌለ ሀይሉን እና ሜካናይዝድ በማደራጀት በአዲስ መልክ ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
መላው የአፋር ህዝብም በተባበረ ክንድ ጁንታውን በሌሎች ወረራ ባካሄደባቸው አካባቢዎችን ያሳዩትን ብርቱ ክንድና ተጋድሎ በኪልበቲ ረሱም በተመሳሳይ መልኩ ወረራውን በመመከት ጁንታው በወረረባቸው አካባቢዎች ሁሉ መቀበሪያቸው ይሆናል! ሲል የክልሉ መግለጫ ደምድሟል።