ዶ/ር ደብረጺዮን ጦርነቱን ለመቋጨት ቡድናቸው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገለጹ ።

የትግራዩ ሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዓል የሰሜኑን ጦርነት ለመቋጨት ቡድናቸው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ለቢቢሲ ዓለማቀፍ ጣቢያ ተናግረዋል።

ተኩስ አቁም ማድረግ በጣም አጣዳፊው ርምጃ እንደሆኑ የጠቀሱት ደብረጺዮን፣ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በሚደረገው የሰላም ድርድር አበረታች ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከተኩስ አቁም በተጨማሪ፣ የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው እና ፌደራል መንግሥቱ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ መፍቀድ እንዳለበት ደብረጺዮን አክለው ገልጸዋል።

ደብረጺዮን ድርጅታቸው ሕወሃት በድርድር ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እየጠየቀ ያለው ከድክመት ሳይሆን ለሰላም ዕድል ለመስጠት እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፣ ቅድመ ሁኔታዎቻችን የማይሟሉ ከሆነ ግን መብታችን ለማስከበር ውጊያ እንቀጥላለን ብለዋል።