ሐኪም በምትፈልግ አገር ሥራ አጥ ሐኪም እንዴት ተፈጠረ ? – የሐኪሞች ሥራ ስጡን እሮሮ

ከሦስት ዓመት በፊት የሕክምና ተመራቂዎች ሥራ በማጣታቸው ተቃውሞ ሊያሰሙ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል። መንግሥት 2011 ዓ. ም. ላይ የሐኪም ምደባ አቁሞ ኃላፊነቱን ለክልሎች ከሰጠ ወዲህ ክልሎች በበጀት እጥረት ሳቢያ በርካታ ባለሙያ ሳይቀጥሩ ቀርተዋል። አሁን ግን የጤና ሚኒስቴር ከበፌት ፋውንዴሽን እና ከክልሎች ጋር በመሆን 350 ሚሊዮን ብር ተመድቦ፤ ለሦስት ዓመታት 2898 ሐኪሞች በክልሎች እንዲቀጠሩ ተወስኗል።

ከሦስት ዓመት በፊት በርካታ የኢትዮጵያ ሐኪሞች ሰልፍ ወጡ።

ደመወዛችን ይጨመር፣ የሚደርስብን የመብት ጥሰት ይገታ፣ የሕክምና ሥርዓቱ ይሻሻል፣ የሕክምና መስጫ ቁሳቁሶች ይሟሉ ከጥያቄዎቻቸው ጥቂቱ ናቸው።

የሕክምና ምሩቆች ጥያቄ ደግሞ እጅግ መሠረታዊው ነው። ሥራ ቅጠሩን!

ሐኪም በምትፈልግ አገር ሥራ አጥ ሐኪም እንዴት ተፈጠረ?

የአማራ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብራራው ታደሰ ከዓመታት በፊት የተስተጋባውን ቅሬታ እንዲህ ያስታውሳሉ።

“ወደእኛ ማኅበር ብዙ ሐኪሞች መጥተው ሥራ ፈልጉልን ይሉናል። ጊዜያቸውን ሰጥተው፣ ወጣትነታቸውን አሳልፈው፣ አገሪቱም ብዙ ገንዘብ አውጥታባቸው ተምረው ሲመረቁ ሥራ አለማግኘታቸው ተቃርኖ ነው። ይፈጠራል ተብሎም አይገመትም።”

ይባስ ብሎ ኢትዮጵያ በርካታ ሐኪሞች ነው የምትፈልገው። ይህ ፍላጎት እያለ የሐኪሞች ሥራ ስጡን እሮሮ ዶ/ር አብራራው እንደሚሉት እውነትም ተቃርኖ ነው።

ሥራ አጥነት በሐኪሞች ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ሕክምና ለመማር በሚመኙ ታዳጊዎች ላይ ጭምር ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ።

ልጆቻችን ተመርቀው ሐኪም ይሆናሉ ብሎ የሚጠብቀው ቤተሰብ፣ በሕክምና ባለሙያ እጥረት ከወሊድ ጋር የተያያዘ እክል የሚገጥማት እናት፣ ሥራ ፍለጋ ከአገር የሚሰደድ ሐኪም. . . የችግሩ መገለጫዎች ብዙ ናቸው።

የማዕከላዊ መንግሥት ምደባ ማቆም

በ2011 ዓ. ም. የጤና ሚኒስቴር ተመራቂ ሐኪሞችን መመደብ አቆመ። በምደባ ምትክ ክልሎች ባለሙያ አወዳድረው ይቅጠሩ ተባለ።

ክልሎች ደግሞ በበጀት እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች በርካታ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ተቸገሩ። ሥራ አጥ ሐኪሞች ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት ደረሱ።

በዚህ ጊዜ ነው የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች እና ከክልሎች ጋር በመሆን ሐኪሞችን በክልሎች የመቅጠር ሐሳብ የጠነሰሰው።

ማዕከላዊ መንግሥት 175 ሚሊዮን ብር ሲመድብ፣ በፌት ፋውንዴሸን የተቀረውን 175 ሚሊዮን ብር ለመሸፈን ተስማምቷል።

በዚህ ገንዘብ፤ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ 2898 የጤና ባለሙያዎች ለሦስት ዓመታት በክልል ከተሞች ይቀጠራሉ።

ዶ/ር አብራራው፤ ይህ አሠራር የሐኪሞችን ሥራ አጥነት ቢያንስ ለተወሰነ ዓመታት ይቀርፋል ይላሉ።

“ሐሳቡን በበጎ እንቀበለዋለን። እንደግፈዋለን። እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ ጥሩ ነው። ዘላቂ መፍትሔ ግን አይሆንም” ይላሉ።

በእሳቸው አስተያየት ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው አገር አቀፍ የጤና በጀት ሲጨመር ነው። ያኔ ክልሎች የመቅጠር አቅማቸውን አሳድገው ብዙ ባለሙያ ማሰማራት ይችላሉ።

አሁን ያለው የጤና ሥርዓት ምን ዓይነት ባለሙያ ይፈልጋል? ተብሎ ሐኪም በዕቅድ እንዲሠለጥን ይመክራሉ።

ከዚያም የሚመረቀውን የጤና ባለሙያ ሊይዝ የሚችል የጤና ተቋም ግንባታ ያስፈልጋል።

በዓለም አቀፍ ደንብ መሠረት አንድ ሐኪም አገልግሎት የሚሰጣቸውን የታካሚዎች ቁጥር ለማመጣጠን የፖሊሲ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት ያምናሉ።

“ክልሎች ሐኪም ይፈልጋሉ። የጤና ባለሙያ ወደእነሱ ሲሄድ ደስ ይላቸዋል። ግን መቅጠር የሚችሉበት ገንዘብ ስለሌለ ክፍተቱ ተፈጠረ” ይላሉ ዶ/ር አብራራው።

ጨምረውም “አሁን ያለው የባለሙያ ቁጥር ለአገሪቱ በቂ አይደለም። ግን ያለውን ባለሙያ ሊቀጥር የሚችል የመንግሥት በጀት የለም። ዋናው ነገር በጀትን ማሻሻል ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ሥራ አጥ ሐኪሞች የሚቀጠሩበት አሠራር

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አማካሪ ዶ/ር ሰናይት በየነ እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት የጤና ባለሙያዎች በብዛት ተምረው ቢመረቁም፤ የሚቀጥሯቸው የጤና ተቋማት የመቀበል አቅም አብሮ አልጎለበትም። እናም ተመርቀው የማይቀጠሩ ባለሙያዎች እየበዙ መጡ።

መንግሥት የሰጠው መፍትሔ ባለሙያዎች ለሦስት ዓመታት በክልል የሚቀጠሩበትን ወጪ ከአጋር ድርጅት ጋር መሸፈን ነው።

ይህ የወጪ መጋራት (Matching Fund) በቀጣይ ዓመታት ሦስት ደረጃዎች እንደሚኖሩት ዶ/ር ሰናይት በየነ ያስረዳሉ።

በመጀሪያው ዓመት ማዕከላዊ መንግሥት እና በፌት ፋውንዴሽን ወጪውን 50/50 ይካፈላሉ። በሁለተኛው ዓመት ክልሎች 25 በመቶ ያዋጣሉ። በሦስተኛው ዓመት ክልሎች 50 በመቶውን ወጪ ይሸፍናሉ።

ከአራተኛው ዓመት በኋላ የባለሙያዎች ደመወዝ ሙሉ በሙሉ በክልሎች እየተከፈለ ይቀጥላል።

“በዘላቂነት የያዝነው ዕቅድ ክልሎች በጀት ይዘው፣ ባለሙያ እየቀጠሩ እንዲሄዱ ማድረግ ነው” ይላሉ አማካሪዋ።

በዚህ ቅጥር በዋነኛነት የሚካተቱት ጤና ሚኒስቴር በክልሎች ምደባ ካቆመበት 2011 ዓ. ም. ወዲህ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ባለሙያዎች ናቸው።

የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ለሥራ ፈላጊዎች በመደበው የበይነ መረብ ገጽ ላይ የሥራ ማመልከቻ ያስገቡ ተወዳድረው ይቀጠራሉ።

ዶ/ር ሰናይት በየነ እንደሚሉት፤ ማቺንግ ፈንድ 75 በመቶ የሚሆኑትን ተመርቀው ሥራ ያልያዙ ሐኪሞች ያስቀጥራል ተብሎ ይታመናል።

“ክልሎች ሊቀጥሯቸው የሚችሉ ሐኪሞች ብዛት ተወስኗል። በዚያ መሠረት በጀት ይተላለፋል። የሚዘረጋው አዲስ መዋቅር አይደለም። በክልል የሚቀጠሩት ሐኪሞች አሁን ባለው የጤና ሥርዓት ይገባሉ። የጤና ሚኒስቴር አሁንም ቢሆን ባለሙያ በክልሎች አይመድብም። ስለዚህ ክልሎቹ አወዳድረው ይቀጥራሉ” ሲሉ ያብራራሉ።

“ሐኪሞችን ለችግር የዳረጋቸው የፖሊሲ መበላሸት ነው”

ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ የጽንስና ማሕጸን ስፔሻሊስት እንዲሁም የሕግ ባለሙያ እና የዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን ፋከልቲና በበፌት ፋውንዴሽን ደግሞ የግሎባል ፕሮግራም ዳይሬክተር ናቸው።

በፌት ፋውንዴሽን ለሦስት ዓመታት የሐኪሞች ቅጥር የሚውል 175 ሚሊዮን ብር መመደቡ፤ ባለሙያዎች ሥራ አጥ እንዳይሆኑ፣ በሙያቸው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉም ያግዛል ይላሉ።

የሚሠለጥኑ ሐኪሞች ቁጥር ሲጨምር የሥራ ዘርፉ ጎን ለጎን አለማደጉን ጠቅሰው “እነዚህን ሐኪሞች ለችግር የዳረጋቸው የፖሊሲ መበላሸት ነው” ይላሉ።

ክልሎች የየራሳቸውን ባለሙያ ይቅጠሩ ሲባል ከበጀት ውስንነት በዘለለ፤ “ከዚህ ክልል ካልሆናችሁ ወይም ቋንቋውን ካልተናገራችሁ አንቀጥርም” ማለታቸው ምስቅልቅል ፈጥሯል።

በዚህ ምስቅልቅል በሺዎች የሚቆጠሩ ሐኪሞች ከቅጥር ውጪ ሆነዋል።

“ሞራላቸው ላሽቋል። ወይ ቤት ነው የሚውሉት ወይም የማይሆን ሥራ ነው እየሠሩ ያሉት” ይላሉ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ።

ማቺንግ ፈንድ ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሆነ ያምናሉ። በቀጣይ ዓመታት የሚመረቁ ሐኪሞች ጉዳይ ከወዲሁ እንዲታሰብብትም ያሳስባሉ።

ሐኪሞች ተሰባስበው በግል ሕክምና መስጫ እንዲከፍቱ ማስቻል፣ ወደ ግል የጤና ዘርፍ በቀላሉ እንዲገቡ ማመቻቸት እና ውጭ አገር መሥራትን እንደ አማራጭ እንዲወስዱ ማድረግ ከፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ ምክሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የሐኪሞች ቅጥር ከዚህ ቀደም እንደነበረው ወደ ፌደራል መንግሥቱ ቢዞር የተሻለ እንደሚሆን ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ ይናገራሉ።

ዶ/ር አብራራው በበኩላቸው ክልሎች በቂ በጀት እስከተሰጣቸው ድረስ የምደባ ኃላፊነት ለእነሱ መተው መሰናክል አይፈጥርም ይላሉ።

የጤና ሚኒስትሯ አማካሪ ዶ/ር ሰናይት በየነ እንደሚሉት ደግሞ፤ ከዚህ በኋላ የክልሎችን በጀት ማሳደግ እንጂ ፌደራል መንግሥቱ ሐኪም ወደመቅጠር የሚመለስበት አሠራር አይኖርም።

“በሙያዬ ያሉ ሰዎች ሥራ አጥተው ማየት ይረብሸኛል”

ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሐ፤ የቤተሰብ ሸክም የሆኑ፣ በራይድ ሹፌርነት የተቀጠሩ፣ የተሰደዱ፣ ሥራ አጥነታቸው ለአእምሮ ሕመም የዳረጋቸው እና ብዙ ልብ የሚሰብሩ የሐኪሞች ታሪኮች ሰምተዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ እና የጥቁር አንበሳ ተማሪዎች የነበሩ የኢትዮጵያ የሕክምና ተማሪዎች ማኅበር አባላት፤ የምርቃት ቀናቸው ሲቃረብ ከመደሰት ይልቅ “ሥራ ላንቀጠር እንችላለን” ብለው ይፈሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከጤና ሚኒስቴር ጋር ወደ ማቺንግ ፈንድ የገቡትም የሙያ አጋሮቻቸው ሥራ አጥተው ማየት ስለረበሻቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

በተለይም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ካለው የባለሙያ ውስንነት አንጻር፤ ኢትዮጵያ የምታስመርቃቸውን ባለሙያዎች በበቂ አለመቅጠሯ ያሳዝናቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለአንድ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል ብሎ የተመነውን የሐኪም ቁጥርን ኢትዮጵያ አታሟላም።

አገሪቷ ለጤና ዘርፏ “ቅድሚያ መስጠት አለባት” ብለው የሚመክሩትም ለዚሁ ነው።

የጤና ዘርፉ መሻሻል አለበት ሲባል የጤና ባለሙያዎች ቅጥር፣ የደመወዝ ማሻሻያ፣ የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠና፣ የጤና ተቋማት ግንባታና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮችን ያካትታል።

መሠረታዊው ነጥብ ግን ሐኪሞችን በአግባቡ፣ በመላው አገሪቱ ማሰማራት መቻል ነው።

ይህ እውን የሚሆው ደግሞ ዘላቂነት ባለው መዋቅራዊ ለውጥ እንጂ ለጥቂት ዓመታት በሚቆይ የክልሎች የቅጥር ስምምነት እንዳልሆነ ያሰምሩበታል።

የክልሎችን የበጀት ውስንነት ከመቅረፍ ባሻገር

ክልሎች የገጠማቸውን የበጀት እጥረት ለማሻሻል ማቺንግ ፈንድ ቢጀመርም፤ የጤና ሚኒስቴር ሐኪሞች ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳቦች እንዳሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አማካሪ ዶ/ር ሰናይት በየነ ይናገራሉ።

አንደኛው፤ የግል ሕክምና መስጫ ለመክፈት በፊት ይጠየቅ የነበረውን የሥራ ልምድ እና ብዙ ኢንቨስትመንት አቅልሎ ሐኪሞች የራሳቸው ማከሚያ (Office Practice) እንዲከፍቱ የሚያስችል አሠራር መጽደቁ ነው።

ሁለተኛው፤ የኢትዮጵያ ሐኪሞች በውጭ አገራት የሚቀጠሩበትን አሠራር ማመቻቸት ነው።

“ብዙ ነገሮች ጎን ለጎን እየተደረጉ ስለሆነ በጊዜ ሂደት ተመርቆ ሥራ የማይዝ የሕክምና ባለሙያ ይኖራል ብዬ አላስብም” ይላሉ።

ክልሎች የባለሙያ ቅጥርን ጨምሮ ለዓመታዊ ወጪ የሚመደብላቸው በጀት ከዓመት ዓመት እያደገ እንደመጣ በማጣቀስ፤ ለወደፊትም እየጨመረ እንደሚሄድ ያክላሉ።

ማዕከላዊ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን በክልሎች መመደብ ሲያቆም ከተነሱ ቅሬታዎች አንዱ፤ ክልሎች ሐኪም የመቅጠር ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው በክልላቸው የሚነገር ቋንቋ የማይችሉ ምሩቃንን ለመቅጠር ማመንታታቸው ነበር።

ዶ/ር ሰናይት በየነ እንደሚሉት፤ ክልሎች ለሐኪም ቅጥር ቋንቋን ዋና መስፈርት እንዳያደርጉ ተመክሯል።