ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዙሪያ የመከረበት መድረክ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ ወደ አገር የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅቶላቸው ሲወያዩ ሰንብተዋል፡፡ በተለይ በኢንቨስትመንት ዙሪያ የዳያስፖራውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ከተዘጋጁ መድረኮች ውስጥ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ያዘጋጀው ይገኝበታል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዴት ይሳተፍ? የሚለው ቀዳሚ ሐሳብ ሲሆን፣ ኢንቨስት ለማድረግ አሉ የተባሉ ችግሮችና መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች የተሰነዘሩበትም ነበር፡፡

ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደኅንነት መረጋገጥ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያደርገው እንቅስቃሴና የሚፈጥረው የሥራ ዕድል አንዱና ዋነኛው ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ ከዚህ አንፃር በተለይ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዙሪያ የመከረበት መድረክ

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፣ በሚኖሩበት ሥፍራ ሁሉ የሚፈጥሩት ሀብት መልሶ ለእናት አገራቸው መጠነ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዙሪያቸው ላሉ አካላት ከሚልኩት የውጭ ምንዛሪ አንስቶ በአገር ላይ በሚፈጥሩት ኢንቨስትመንት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ እንደ ንግድ ምክር ቤት እንደሚገነዘቡ የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ በተለያየ የትምህርት ደረጃና ሙያ በመሰማራት፣ ቴክኖሎጂን ወደ አገር በማስገባትና እንዲተዋወቅ በማድረግ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን በማሳደግ የኢኮኖሚው አለኝታ መሆናቸው ግነት እንደማይሆንም አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ትልቅ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከተፈለገ በርካታ እግሮች መስተካከል እንደሚገባቸው በዕለቱ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተሰነዘረው አስተያየት ነው፡፡

ዳያስፖራውና ጥያቄው

ከዕለቱ የውይይት መድረክ መገንዘብ እንደተቻለው፣ ዳያስፖራው በአገሩ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አለው፡፡ ነገር ግን ይህንን ፍላጎት በተግባር ለመቀየር መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በዕለቱ አስተያየታቸውን ከሰጡ ዳያስፖራዎች መካከል ከኢትዮጵያ ከወጡ 40 ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ ግርማ መርጊያ አንዱ ናቸው፡፡ አሁን እየታየ ያለውን የዳያስፖራው ኅብረትና የአገር ፍቅር ስሜት የሚያስደስት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡  ከውጭ ሲመጡ ‹‹እንኳን ወደ አገራችሁ በሰላም መጣችሁ›› መባሉ ትልቅ ነገር መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በአሜሪካ በነበሩበት ወቅት ለአገራቸው የተጠየቁትን ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ግርማ፣  ለግድብ፣ ለድርቁም መርዳታቸውን ነገር ግን ዳያስፖራው ሁሌ የሚታየው ከውጭ ምንዛሪ አቅም አንፃር እየመሰለ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ይገልጽልኛል ብለው በምሳሌነት ያነሱት፣ ‹‹እኔና ባለቤቴ 230 ሺሕ ዶላር አፓርትመንት ዩኒት ገዛን፡፡ ቤቱ እየተከራየ ገንዘቡን እናስቀምጣለን፡፡ ዩቲዩብ ላይ ባንኮች ሼር ይሸጣሉ የሚል ስለሰማሁ ይህንን ተከትዬ ሄጄ አንተ የሎ ካርድ ስላለህ መግዛት ትችላለህ ተብሎ በብር ሼር ገዛሁ፡፡ ሆኖም በኋላ ላይ የውጭ ዜግነት ያለው አይገዛም ተብሎ የገዛሁት አክሲዮን ተመላሽ ተደረገ›› ይላሉ፡፡

ዳያስፖራውን እናስተናግድ ሲባል እንዲህ ያሉ ነገሮች መስተካከል ይገባቸዋል በማለት ለምን ይህ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኛ ክልል የሌለን ኢትዮጵያውያኖች ምን እንሁን?›› በሚል ጥያቄ የጀመሩት ሌላው የዳያስፖራ አባል ደግሞ፣ በየክልሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚገጥመው ችግር እንደሚያሳስባቸው አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ መታየት ያለባት እንደ አንድ መሆኑንም ገልጸው፣ ‹‹እኔ ካሊፎርኒያ ብኖር ነገ ሄጄ ጆርጂያ ልኖር እችላለሁ የሚጠይቀኝ የለም፡፡ ለምን መጣሽ የሚለን የለም፡፡ በአገራችን በተወለድንባት ኢትዮጵያ በየቦታው ማንነታችን መጠየቅ የለበትም፣ መሥራት ነው የምንፈልገው፤›› በማለት አለ ያሉትን ችግር ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል ለምን ኢንቨስት አያደርጉም ከሚለው ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹በአገር ውስጥ ገብተን ብንሠራ መጤና ከውጪ የሚባል አስተሳሰብ አለና እንዴት አድርገን ነው ንብረት እዚያ ላይ ማስፈር የምንችለው፣ እንዴትስ አድርገን ነው ይህንን ቢሮክራሲ ልንሻገር የምንችለው፡፡ እዚያ ላይ ንብረት አስፍረን ደግሞ ንብረታችን ሊወድም ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ክልል የየራሱ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አለው፡፡ እያንዳንዱ ክልል ደግሞ የራሱን ዘር ነው የሚፈልገው፡፡ እንደ አገር አንድ ወጥ የሆነ አሠራሮች ያስፈልጉናል›› ብለዋል፡፡

ውጭ ያለው ኅብረተሰብ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በተለየ ለመሥራት ፍላጎት ያለው ነው ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ችግሩ የአገር ውስጥ የፖለቲካ መዋቅር መሆኑን፣ መዋቅሩ እንደማይጋብዝ፣ ይህ ካልተስተካከለ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

‹‹በደንብ ትቀበሉንና ለዘራፊ ትሰጡናላችሁ›› ያሉም አሉ፡፡ በተለይ ቢሮክራሲው በጣም አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በጣም ሙስና መኖሩም ተነስቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ሌሎች ችግሮች፣ ጥያቄዎችና አስተያየቶች፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችም ተነስተዋል፡፡ የብዙዎቹ ሐሳብ መሥራት እንፈልጋለን ግን ቢሮክራሲውና ሙስናው መጥፋት አለበት የሚል ነው፡፡

የኮሚሽነሩ አስተያየትና ምላሽ በዝርዝር ይህን ተጭነው ይመልከቱት