ፖሊስ በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ላይ የጅምላ መቃብር አገኘሁ አለ።

BBC AMHARIC

ፖሊስ በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ላይ የጅምላ መቃብር አገኘሁ አለ።ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ የጅምላ መቃብሮቹ የ200 ሰዎች አስክሬን ይዘዋል። ፖሊስ ይህን ያለው የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሐመድ ዑመር በፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ትናንት በቀረቡብት ወቅት ነበር።ፖሊስ ጨምሮም የሟቾችን ማንነት ለማጣራት እየሰራ መሆኑ ተናግሯል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅሟል በማለት የፌደራል መንግሥት ቡድኑን በአስቸኳይ እንዲበትን ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አምነስቲ ልዩ ፖሊስ ሰዎችን ከመግደል እሰከ መኖሪያ ቤቶችን ማጋየት የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ፈጽሟል ብሎ ነበር።

ሌላው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች ከወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ በሶማሌ ክልል በሚገኘው ኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ታሳሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች እና የልዩ ፖሊስ አባላት ድብደባ እና የመደፈር ጥቃት እንዳደረሱባቸው ገልጿል። ሂዩማን ራይትስ ዋች ካነጋገራቸው ሴቶች መካከል በእስር ቤቱ ውስጥ ተደፍረው እዚያው በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ያለ ህክምና ዕርዳታ ልጆቻቸውን እንደተገላገሉ ገልጸዋል።

የተለያዩ አካላት ልዩ ፖሊስ በክልሉ እና በአካባቢው ለተፈጸሙ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈሮችና መፈናቀሎች ተጠያቂ ይደረጋሉ። ልዩ ፖሊሰ ተጠሪነቱ ለቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሐመድ ዑመር እንደሆነም ይታመናል።

ከልዩ ፖሊስ በተጨማሪ ሄጎ በመባል የሚታወቀው ቡድን በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተሳትፎ እንዳለበት ፖሊስ ገልጾ ነበር።

ሐምሌ 27፣ 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ሃይማኖር እና ብሄርን መሰረት አድርጎ በተፈጸመ ግድያ 96 ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል። በወቅቱ የቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ለቢቢሲ ሲናገሩ “በዋናነት በግጭቱ ተሳትፈዋል የሚባሉት ሄጎ የሚባለው ቡድን አባላት ናቸው። ሄጎ የሚባለውን የፈጠሩ፣ እቅዱን ያቀነባበሩ የክልሉ የፖለቲካ አመራሮች፣ የክልሉ የካቢኔ አባላትና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየሰራን ነው” ብለው ነበር።

በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ ፖሊስ እስካሁን በሶማሌ ክልልና አካባቢው በተፈጸመውን ወንጀል ጉዳት የደረሰባቸውን ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ የተጎጂዎችን የህክምና ማስረጃ ማሰባሰቡን ለፍርድ ቤቱ በማሳወቅ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን ተጨማሪ የምረመራ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተጨማሪ የምረመራ ጊዜውን ፈቅዷል።

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE