ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጉዳይ የግላቸውን አቋም እንዳያንጸባርቁ በተመድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ጽ/ቤት ጠየቀ

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፥ ” እንደ ዓለም ጤና ድርጅት አይነት ለሁሉም ሰው በእኩል ቆመናል የሚሉ አለምአቀፍ ተቋማት ግን አሸባሪው ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ሀስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዙ አልተደመጡም ይልቁንም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል የአሸባሪው ቡድን የሚያሰማውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው እያስተጋቡት ይገኛል። ይህ በመንግስት ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ” ሲል አሳውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጉዳይ የግላቸውን አቋም እንዳያንጸባርቁ ኢትዮጵያ ጠየቀች፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ትናንትና ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ አግዷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግስት በራሱ ዜጎች ላይ ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ድጋፎችን እንዳያገኙ እገዳ ጥሏል ሲሉም ነበር ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ይህን ተከትሎ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ፖለቲካዊ ውግንና አላቸው ያላቸው ዶ/ር ቴድሮስ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁና ገለልተኛ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡

የተሰጣቸውን ዓለም አቀፋዊ ሚና ከመወጣት ይልቅ ከፖለቲካዊ እና ግለሰባዊ ፍላጎት የመነጨ ውግንናቸውን እያንጸባረቁ ነው ያለው ጽህፈት ቤቱ የተመድ ኤጀንሲዎች ስራም በዚሁ ምክንያት እየተስተጓጎለ ይገኛል ብሏል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ የትኞቹም ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁም ነው በተመድ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ጽ/ቤት የጠየቀው፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የጤና ተቋማት ሲወድሙ ምንም አላለም በሚል የዓለም ጤና ድርጅትን መውቀሷ ይታወሳል።

ዛሬ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቶ ነበር።

በዚህም መግለጫው ላይ TPLF ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን አስገንዝቧል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፥ ” እንደ ዓለም ጤና ድርጅት አይነት ለሁሉም ሰው በእኩል ቆመናል የሚሉ አለምአቀፍ ተቋማት ግን አሸባሪው ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ሀስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዙ አልተደመጡም ” ብሏል።

” ይልቁንም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል የአሸባሪው ቡድን የሚያሰማውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው እያስተጋቡት ይገኛል። ይህ በመንግስት ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ” ሲል አሳውቋል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፥ ” አሁንም ለአንድ ወገን ባጋደለው አቋማቸው በመጽናት የሽብር ቡድኑ ወደ ትግራይ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት መሆኑን በግልጽ አለማንሳታቸው በተዛባ አመለካከታቸው መጽናታቸውንና ውግንናቸው ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለፖለቲካ አጀንዳ መሆኑን ያመለክታል ” ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ክልል ህዝብ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲቀርብ ለማስቻል በየጊዜው ከአጋር አካላት ጋር ምክክሮችን በማድረግ እየሠራ ይገኛል ሲል አሳውቋል።