እርቅን ማውረድ የጠንካሮች ፤ እርቅን ማጨናገፍ የደካሞች ባህርይ ነው!

እርቅን ማውረድ የጠንካሮች ፤ እርቅን ማጨናገፍ የደካሞች ባህርይ ነው!

እርቅ ሲርቅ ፤ ቀልብ ይሰርቅ

በግልጽ እንደሚታወቀው በዋሽንግተን ዲሲ የርዕሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ውስጥ የዛሬ ሶስት አመት የተቀሰቀሰው ግጭትና ያስከተለው የርስበርስ ያለመግባባት ችግር እጅግ የሚያሳዝንና  ቤተክርስቲያናችንንና መላው ምእመናንን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለና እያስከፈለ ያለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን መፍትሄው ከሰማይ እርቆ ሳይሆን ቅንነተ በመጥፋቱ ብቻ እየቀጠለ ያለ በእጅጉ የሚያስቆጭ ድርጊት ሆኖ ይገኛል። ይሁንና ዛሬም እንደትናንቱ የችግሩን መንሰኤ አንስቶ ጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት የዚህ ጽሁፍ አላማ አለመሆኑን አስቀድመን ለመግለጽ እንወዳለን። አሁን ይህን ጉዳይ በዚህ ስዓት ማንሳትና መመለስ የምንፈልገው ለምንድነው ቢባል የተፈጠረውን አለምግባባት እስከዛሬ በእርቅና በውይይት መፍታት ያልተቻለው ለምንድን ነው የሚለው አብይ ጥያቄ መልስ ማግኘት ስላለበት ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ከዚህ በፊት ጥቂት የተሞከሩና ጨንግፈው የቀሩ የእርቅ ሂደቶችን እንጠቃቅስና ዛሬ የምንገኝበትን ታሪካዊ ሁኔታ እንቃኛለን።

የመጀመሪያው እርቅ መፍረስ:

የቤተክርስቲያናችን ችግር ከሰባት አመት በላይ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ የዛሬ ሶስት አመት ፈንድቶ ያን የመሰለ አሳፋሪ ጉዳይ ሲከሰት ብዙ ሰዎችን በማሳዘኑና አልፎም በማስጨነቁ ችግሩ የተፈጠረ ሰሞን የተለያዩ ወገኖቻችን ችግሩ ሳይባባስ በእንጭጩ ለመቅጨት ይቻል ዘንድ የማስታረቅ ሙከራ ለማድረግ ላይ ታች ቢሉም የትም ሊደርስ ሳይችል ሲቅር በስተመጨረሻ ሁሉም ተቆርቋሪዎች በአንድነት ጠንከር ብለው የጅመሩት የማስታረቅ ጅምር እራሳቸው አስታራቂዎቹ እርስ በርሳቸው መግባባት ባለመቻላቸውና እነርሱን የሚሸመግል ሌላ አስታራቂ በመጥፋቱ የእርቁ ጥረት ተጭናገፈፎ በጅምር ቀረ:: ትንሽ ሰነባብቶ እንደሰማነው የችግሩ መነሻ ሰብሳቢ ብለው የመረጧቸው ግለሰብ ገና ከጅምሩ ግልጽ የሆነ አድሎዊነት በማሳየታቸውና እርሳቸውም ከአድርጎታቸው ሊታቀቡ ስላልቻሉ የሽምግልናው ሂደት ሊደናቀፍ እንደቻለ ነው።

የሁለተኛው እርቅ መፍረስ:

ሁለተኛውና ሁሉንም በደስትታ ሲቃ ያስለቀሰውና እፎይታን ለአጭር ጊዜም ቢሆን የፈጠረው በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ቀን ውሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው ታሪካዊው የሁለትዮሽ ሰምምነት ነበር። ስምምነቱ በወቅቱ አዲስ የቦርድ ምርጫ እንዲደረግ የሚል ሲሆን በተከሳሽ ወገን የሚገኙትና በህጉ መስክ ጥሩ የሚባል እውቀትና ተሞከሮ ያላቸው ግለሰብ በእለቱ ለተካሳሾቹና ለደጋፊዎቻቸው በግለጽ እንዳስረዷቸው ከድርድሩ ከሚፈለገው በላይ እንደተገኘ ገለጸው ውጤቱን አለማወላወል መቀበል እንደሚገባ መግለጻቸውን ስምተናል። በእኛም በኩል የቤተክርስቲያናችን ችግር እንዳይባባስና ነገሩን በእንጭጩ ማቆም የሚገባ ነው ብልን በማመናችን የጠየቁትን ሙሉ በሙለ በሚባል መልኩ በመቀበል የቦርድ ምርጫ በአንድ ሳምንት ለማካሂድ ተስማምተን እንደነበር ሁሉም ወገን የሚያውቀው ሀቅ ነው። በማግስቱ የደረስን መልዕክት በእጅጉ በጣም ልብ የሚሰብር ነበር። በድርድሩ የተሳትፉት አምስት ሰዎች የተደረገውን ስምምነት ሲቀበሉት የተቀሩት አስራ ስምንት ሰዎች ተቃውመውት የቤተክርስቲያናችን ችገር ከመቃለል ይልቅ በከፋ መልኩ  እንዲቅጥል ሆነ። የተደረሰው እርቅ ቤተክርስቲያኗን ማዕከል ያደረግ ስለነበር የአንዳንድ ወንድሞቻችንን የተለየ ፍላጎት ሊያሳካ ባለመቻሉ  እርቁን ወድቅ አደረጉት። የፍርድ ቤቱ ጉዳይ የተጀመረ እለት ማለቅ ሲችል ምክንያቱ ለእኛ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በእነዚህ ግለሰቦች ፍላጎት ክሱ እንዲቀጥል ተደረገ። እነዚህ ወገኖች  በእርቁ ላይ ቅሬታ ካላቸው ማሻሻያ መጠየቅ አልያም ቀረ የሚሉት ካለ እንዲካተትላቸው ከመጠየቅ ይልቅ የመረጡት መንገድ ውድ የሆነ ጠበቃ ማፈላለግና የቤተክርስቲያኗን ጣር ማስቀጠል ነበር። እኛም ምን እንደሚፈልጉ ግልጽ ባልሆነልን ሁኔታ ስለፈለግነው ሳይሆን እነርሱ ስለፈለጉት ብቻ በፍርድ ሂደቱ እንድንቅጥል ተገደድን።  ይህም እኛንም ሆነ መላውን  ምዕመናኑን በእጅጉ አሳዝኗል።

የሶስተኛው እርቅ መፍረስ

ሶስተኛው የእርቅ ሂደት ደግሞ ዳኛ ሮስ በአንድነት ሆናችሁ በስምምነት አምልኩ ካልፈለጋችሁ ግን ቤተክርስቲያኑን እዘጋዋለው ሲል በመጀመሪያ ቤተክርስቲያናችን መዘጋት የለባትም ብለን ድምጻችንን ያሰማነው እኛ መሆናችንን በጊዜው የነበረ ሁሉ ያውቀዋል። ይህንንም ተከትሎ ዳኛው ከኛ አንድ ከተከሳሽ ወገን አንድ እንዲሁም ከሁለታችን ውጭ የሆነ ሶስተኛ ሰው ተመርጦ ቤተክርስቲያኑ ለጊዜው በሶስቱ ሰዎች ይተዳደር ሲል በእኛ በኩል የዳኛ ሮስን ሃሳብ ስንቀበል በእነርሱ ወገን ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት ይህም ጥረት ሳይሣካ ቀርቶአል።

የአራተኛው እርቅ መፍረስ

በተለያየ ጊዜ በጠበቃቸው በኩል የቦርድ ምርጫ እንዲደረግ ፈቃደኝነታችንን ስንጠየቅ ሁሌም መልሳችን በችግሩ ጊዜ  የነበሩትን አባላት ያካተተ ምርጫው ይደረግ የሚል ነበር። ይህን የምንለው ሁለቱንም ወገን ሊያስማማ የሚችለው በጊዜው የነበረው አባላት ብቻ በመሆኑ ነበር። የቦርድ ምርጫ መደረግ ካለበት በጊዜው በነበሩት የቤተክርስትያኒቷ አባላት ይሁን ስንል ምክንያታችን ከግጭቱ በኋላ ብዙ አዳዲስ ኣባላት በሁለቱም ወገን እየተመለመሉ በመሆኑ በቀላሉ ሊያስማማ እንደማይችል ስለምናምን ነበር።  እኛ የሰጠናቸውን አማራጭ ተቀብሎ እየተነጋገሩ አስፈላጊ ማሻሻዮችን ማድረግ ሲቻል እኛ ጠይቀናቸው አነሱ እምቢ አሉ ለማለት ብቻ በሚመስል መልኩ የሚደረግ ስለነበር ንግግሩ ሁሌም እንደተጀመረ ይቆም ነበር። ሁለታችንን በሚያስማማን (common ground) ላይ ሆነን ምርጫውን እናካሂድ ከማለት ውጭ ሌላ አማራጭ ስላልነበረንና ከተከሳሾችም ወገን የሚቀርብ የሚያስማማ አማራጭ ስላልነበረ ይህም የትም ሊደርስ አልቻላም። ጠበቆቻቸው የሚሉን ደንበኞቻቸው የሚፈልጉትንና መስፈርት ያለምንም ቅድመሁኔታ እንድንቀበል ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ መቼም ተቀባይነት የሚያገኝ አማራጭ አልነበረም።

የአምስተኛው እርቅ መፍረስ

ሌላውና በቅርቡ የሆነው አሳዛኝ ክስተት የፍርዱ ሂደቱ ወደ ይግባኝ ከተዛወረ በኋላ በየግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጠያቂነት የተሞከረው የእርቅ ሂደት ነበር። በተለምዶ ሁሌም አንድ ዳኛ ጉዳዩን በፍርድ ሂደት ከማየቱ በፊት ሁለቱም ወገኖች ከሳሽና ተከሳሽ ጉዳዩን በእርቅ ለመፍታት ይሞክሩት እንደሆነ የሚጠይቅበት አካሄድ በመኖሩ አዲሱ የይግባኝ ሂደት ከመጀመሩ በፊት በዳኛው ጽ/ቤት በኩል ተመሳሳይ የእርቅ ጥያቄ ቀርቦልን ነበር። እኛም በጠበቆቻችን በኩል ይሄው ተነግሮን ከተወያየንበት  በኋላ በጠበቆቻቸን ግፊት ጥያቄያችንን ከወትሮ ዝቅ በማድረግ ለእርቁ ያለንን ፍላጎታችንን ገለጽን። ጥያቄያችንን ዝቅ ያደረግንበት ምክንያት ጠበቆቻችን ለድርድር ይዘን የምንቀርበው በፍርድ ቤት በተያዘው መጠን ከሆነ ነገሩ ሳይጀመር በፍርድ ቤቱ ጽፈት ቤትም ሆነ በሌላኛው ወገን ከልብ እንዳልሆንን ያሳያል ስለተባልን ነበር በጣም ዝቅ ያለ የመደራደሪያ ነጥብ ያቅረብነው። አባሎቻችንን ሰለታሰበው የእርቅ ሀሳብ በጊዜው ስናወያያቸው ፤ በርግጥ ዋናው ጥያቄ የቤተክርስቲያን ስራዐት የመከበር ጉዳይ ቢሆንም ለሰላምና እርቅ ሲባል ፣ ስለሃገር ሲባል፣ አብረን የኖርንና ወደፊትም የማንለያይ ስለሆነን በዚህ እንስማማ በሚል የተቀበሉት ጉዳይ ነበር። ሆኖም አለመታደል ሆነና ከጥቂት ቀናት በሁዋላ  በጠብቃችን በኩል የተነገረን መልስ እጅግ የሚያስደነግጥና እነዚያ ወገኖቻቸን ለኛ ያላቸውን ከፍተኛ ጥላቻ የሚያሳይ እንደነበረ ስናይ ከመቼውም በተለየ መልኩ በጉዳዩ ላይ ተስፋ ቆረጥን። ይህ ጥላቻን፣ ንቀትንና አብረን ለሩብ ዓመታት ያሳለፍነዉን ውጣውረድ ያላገናዘበ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር መልስ ነበር። የእርቅ ሂደቱ እንደገና በመታሰቡ በእጅጉ የተደሰቱትም አባሎቻቸን ክፉኛ አዘኑ። ለብዙ ጊዜ ሲጠይቁት የነበረውንና በቤተክርስቲያናችን አስተዳደርና ቦርድ የሚሰጣቸውን ተስፋ አምነው ለጊዜው ያቆዩትን የአምልኮ መብታቸውን የመጠየቅ የክስ ሂደት እንደሚጀመሩ በአንደነት ወሰኑ።

ቤተክርስቲያናቸውን በጫካ ህግ አፍርስውባቸው ፣ ከጥፋተኞች ጋራ ባለመተባበራቸው ብቻ ከየት እንደተሰባሰቡ በማይታውቁ እራስቸውን ግብረሀይል ብልው በሚጠሩ ህይሎች (mercenaries) ለ27 ዓመት ከኖሩባት ቤተክርስቲያናቸው  እንዳይገቡ የታገቱት አባላት መብታቸውን ለመጠየቅ ወደ ህግ ቢሄዱ ብዙ የሚደንቅ አይሆንም። መዘንጋት የሌለበት እነዚህ ምዕመናን ዛሬም እንደትናንቱ በፍቅርና በሰላም የማምለክ መብታቸውን እየጠየቁ ያሉ ማንንም የማይጠሉ ከማንም ከምንም በላይ ሃይማኖታቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን የሚወዱ የቤተክርስቲያናችን የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው። ጉዳዩ እነርሱ ይህንን ክስ ለምን መሰረቱ ብሎ የሰላሙን ሂደትና ጥረት ማቆም ሳይሆን ኃይማኖታችን እንደሚነግረን ጥልን በፍቅር ለማሸነፍ፣ ቀርቦ ችግራቸዉን በመረዳት የነዚያን ወገኖቻችውን ችግር ሊፈታ የሚችል ሰላም መፍጠር ነው ።

መቼም ቢሆን መብትን በህግ መጠየቅ ነውር የሚሆንበት ጊዜ ያለ አይመስለንም። የቆመን ታቦት ረግጦ፤ የተከበረን ኦውደ ምህረትን አርክሶና የጸሎትና የምልጃ ስፍራን መሰዳደቢያና መደባደቢያ አድርጎ በጫካ ሀግ መብትን ማስከበር ሲቻል መብታችሁን በሰላማዊና በህግ ለምን ጠየቃችሁ የሚል ወገን ካለ እርሱ እራሱን እንደገና መለስ ብሎ መመርመር ያለበት ይምስለናል። “እነሱ ገንዘብ ነው የሚፈልጉት፤ እኛ ደግሞ አንዲት ሳንቲም አንሰጣቸውም” እያሉ መፎከሩ የጉዳዩን ጥልቀት  አለማወቃቸውን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየው የቆሙበትን አውድ የማይመጥን አስተዛዛቢ ንግግር እንደነበረ ነው። እኒህ አባላት ትናንትም ዛሬም ነገም ፍትህን እስከሚያገኙና እውነት እስክትገለጥ ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት የሚከፍሉ የቤተክርስቲያናችን የቁርጥ ቀን ልጆች ሲሆኑ ለዚህም የህዝብን ገንዘብ ሳይሆን የራሳቸውን  ገንዘብ ፤ ጊዜና ጉልበት መስዋእት እያደረጉ ያሉ ስለሆኑ “እነርሱ ሳንቲም ነው የሚፈልጉት” ብሎ ርካሽ ወሬ ማውራት እራስን ከማርከስ ውጪ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን በፍጹም አይችልም።

እንግዲህ ከላይ የጠቅስናቸውን የሰላም ጥረቶች በማንና እንዴት እንደከሽፉ በአጭሩ ለማየት የሞከርነው ዛሬም እንደትናንቱ የተጀመረውን መልካም የእርቅ ሂደት ጥቂቶች ውኃ ሊቸልሱበት ሲገዳደሩ ስናይ ዝም ማለት እንደማይገባን በማሰብ ነው። በአሁኑ ሰዓት እጅግ በጣም ቅንና ለሃይማኖታቸውና ለቤተክርስቲያናቸው ቀናኢ በሆኑ ሰዎች ከሰደስት ወር በፊት የተጀመረ አንድ የእርቅ ሂዲት አለ። እኒህ ግለስቦች ለየስሙላ ሳይሆን ከልባቸው እርቁን ከግብ ለማድረስ የተነሱ በመሆናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ሁለቱን ቦርዶች ለማገናኘት እጅግ የተሳክ ጥረት አድርገው የመገናኛው ቀን ተቆርጦ ሁለቱም ወገኖች ቀኑን እየተጠባበቁ እያለ ክስ ተመሰረተብን በሚል ስንካላ ምክንያት የመጀመሪያው የሁለቱ ወገኖች የፊት ለፊት ውይይት ሊስተጓጎል ችሏል። እርቁን የማይደግፉ ኃይሎች  “እነርሱ ድሮም እርቅ አይፈልጉም። እርቅ እያሉ በጎን ይከሱናል። በተደጋጋሚ ለእርቅ ሲጠየቁ እንቢ ብለዋል”  የሚሉና ሌላም ሌላ ክሶችን እንደምክንያት በማንሳት የእርቁን ጥረት ለማክሽፍ ደፋ ቀና ሲሉ እየታዘብናቸው ነው።  የእነዚህ ሰዎች ክስ እውነት ከሆነ መቼና የት እኛ እርቅ ረግጠን እንደውጣን ቢገልጹልን መልካም ነው። ከላይ በዋቢነት ከአንድ እስክ አምስት እንዳሳየነው በየትኛውም ጊዜ እኛ ለእርቅ ጀርባችንን የሰጠንበት ጊዜ የለም። አሁንም ቢሆንም እኛ ሳንሆን ተከሰስን የሚሉ ወንድሞቻችን ናቸው የእርቅ ውይይት ላይ አንገኝም ያሉት ። በኛ እምነት ማንኛውም ችግር መፍትሄ የሚያገኘው እኛና እናንተ ቁጭ ብለን ተወያይተን ስንፈታው ነውና  ዛሬም በውይይቱ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን እየጠበቅናችሁ የምንገኝ እንጂ ድርድሩን ለማፍርስ ደፋ ቀና እያልን ስላልሆነ ድርድሩን ረግጦ ለመውጣት እኛን ምክንያት ባታደርጉን መልካም ነው።

ማንም እነርሱ ለእርቅ ዝገጁ አየደሉም እያለ በእኛ ስም የራሱን ድብቅ አጀንዳ እንዲያሳካ አንፈቅድለትም። ለእርቁ ያለንን ዝግጁነት እኛን እንጂ ማንም መጠየቅ አይኖርበትም። በእርቅ የሚጠቀሙ እጅግ ብዙ የቤተክርስቲያናችን ልጆች እንዳሉ ሁሉ ጥቂቶች በቤተክርስቲያናችን ችግርና በተፈጠረው ግርግር የተጠቀሙ ወይንም እንደተጠቀሙ የሚያስቡ እንዳሉ  በማሰብ ይህ የተጀመረ የእርቅ ሂደት በእንደዚህ እይነቶቹ ግለኞች እንዳይሰናከል መጠንቀቅ አለብን።  ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ባለፈው ጊዜያት ብዙ ጥሩ የሚባሉ የሰላም አጋጣሚዎች አምልጠውናል። ከነዚያ ስህተቶች ተምረን ጠንክረን መውጣት  እንጂ ሁሌም መልካም ጥረቶችን እንዳይሳኩ በሚያደርጉ ድኩማኖች መሸነፍ አይኖርብንም። የቤተክርስቲያናችን ችግር የሚፈታው እኛ ልጆችዋ እንደ ከርስቲያንና እንደ አንድ የሀገር ልጅ ቀና ሆነን በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ላይ ቁጭ ብለን በችግሮቻችን ላይ ስንመክር እንጂ  አውድ ምህረት ላይ እየወጣን ይበልጥ የሚከፋፍለንንና የሚያፋጀንን በመስበክ አይሆንም።

በመጨረሻም “እነርሱ እንዲህ ናችው.፤ እንዲያ ናችው” ከሚለው ተራ ነገር ውጥተን ክርስቲያንነታችንን በሚመጥን መንገድ ከሶስት አመት በፊት በቤተክርስቲያናችን የተከሰተውን አስነዋሪና አሳፋሪ ድርጊት ዛሬ እኛ እግዚአብሄር እድሉን የሰጠን ልጆቹ በመንፈስም በጸሎትም በርትተን ለአንዴም ለሁሌም እናስተካክለው። ትልልቁ የቤተክርስቲያናችንና የህገራችን ችግሮች በጠንካራ የህገራችን ልጆችና አባቶች ሊታመን በማይቻል መልኩ ተፈቶ እያየን ጥቂቶች ስላልፈለጉት ብቻ እርቁ እንዲመክን ካደረግነው እናት ቤተክርስቲያናችንም ሆነች ታሪክ ይቅር አይለንም። እርቅ ሲርቅ ፤ ቀልብ ይሰርቅ ነውና አምልኮታችን ከልብና ከቀልባችን ይሆን ዘንድ ፤ የተጋረጠብንን የጠብ ግርግዳ በእርቅ ፈተን፣ በሰላምና በፍቅር እግዚአብሄርን እንድናመልክ ለውይይትና ለርቅ እንትጋ ስይጣንንም ድል እንንሳው።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

አሜን!!!

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE