ለወራት በውሃ ጥም ስትቃጠል የከረመችው ሐረር በፈረቃ ውሃ ማግኘት መጀመሯ ተሰምቷል

ለወራት በውሃ ጥም ስትቃጠል የከረመችው ሐረር በፈረቃም ቢሆን ውሃ ማግኘት መጀመሯ ተሰምቷል።

ባለፈው ሳምንት ሐረር ከተማ ያሉ ሰፈሮች እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ ውሃ ሳያገኙ እንደቆዩ መዘገባችን ይታወሳል፤ የሐረር ከተማ ሰዎችም የድረሱልን ጥሪ አቅርበው ነበር።

የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የከተማዋ አንድ ሦስተኛ ክፍል የቧንቧ ውሃ ማግኘት ጀምሯል።

«የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የነበረው የዓለማያ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከኦሮሚያ መስተዳድር እና ከዓለማያ እና አወዳይ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ጣቢያው አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥል ተደርጓል» ይላሉ ባለስልጣኑ።

አክለውም «ከዓለማያ የሚመጣውን ውሃ ከድሬዳዋ ከሚመጣው ጋር በማጣመር ቢያንስ የከተማዋን አንድ ሦስተኛ ክፍል በማዳረስ ለማረጋጋት እየጣርን ነው» ብለዋል አቶ ተወለዳ።

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ደግሞ ሌሎች ውሃ ያልደረሳቸውን ቦታዎች በፈረቃ የማዳረስ ዕቅድ እንዳላቸው ባለሥልጣኑ አሳውቀዋል።

የኤረር የውሃ መስመር ችግር እስካሁን እንዳልተፈታ የጠቆሙት አቶ ተወለዳ በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ቀናት ችግሩ እንደሚቀረፍ እምነት አላቸው።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያሰቡት ነገር እንዳለ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ «ሌሎች ውሃ አመንጪ ጉድጓዶች ቆፍረን መስመር ለመዘርጋት ዝግጅት ላይ ነን» ብለው፤ ወደ ሐረር ከተማ ውሃ የሚያሰራጩ መስመሮችን በማብዛት ሥራ መጠመዳቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም «ለሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታት ከተማዋ ምን ያህል ውሃ ያስፈልጋታል የሚል ጥናት ልናካሂድም ነው» ብለዋል።

አቶ ዳንኤል በርሄ በሐረር ከተማ የሆቴል ባለቤት ናቸው። ላለፈው አንድ ወር በሳምንት ከግለሰብ ከቦቴ ውሀ በ2000 ብር እንደገዙ ያስታውሳሉ።

አሁን ግን ውሃ መጥቶ «ትልልቅ ማጠራቀሚያቸውንም ባሊውንም ሞልተናል» ይላሉ፤ ሌሎች ከእርሳቸው ሰፈር በከፋ ለአራት ወራት ያክል ውሃ ያላገኙ ሥፍራዎች እንዳሉ በመጠቆም።

ችግሩ ፀንቶባቸው የቆዩ ቦታዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የውሃ አቅርቦት እንዲኖራቸው መደረጉን ባለሥልጣኑ አክለው ነግረውናል።

«ቅድሚያ የሰጠናቸው ለረዥም ወራት ውሃ የሚባል ያላገኙ አካባቢዎችን ነው፤ ለምሳሌ በተለምዶ ጊዮርጊስ ጋራ እና ከራስ ሆቴል በላይ ያሉ አካባቢዎችን ነው። ከራስ ሆቴል በታች ያሉትም ቢበዛ በአራት ቀናት ውስጥ ውሃ እንደሚያገኙ እምነቴ ነው» ብለዋል አቶ ተወለዳ።

ባለስልጣኑ አክለውም «10 ሚሊዮን ብር ካልተሰጠን የዓለማያ ውሃ ጣቢያ አግልግሎት እንዲሰጥ አንፈቅድም ያሉ ሰዎችን አደብ በማስያዝ የኦሮሚያ ክልል አስተዋፅኦ አበርክቷል» ይላሉ።

የሐረር ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ችግራቸውን ለማስታገስ የታሸገ ውሃ በመግዛት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልፀውልን እንደነበር አይዘነጋም።

ውሃ ሲጠፋ 55 ኪሎ ሜትር ድረስ ተጉዘው የሚቀዱ እንዳሉ እና ይህንን ማድረግ የሚችሉት መኪና ያላቸው እንደሆኑም የችግሩን ግዝፈት እንደሚያሳይ ተነግሮ ነበር።