በመዲናዋ ያለው አጠቃላይ ድባብ ሰላማዊ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ መዲና የዕለት ተዕት ሕይወት ላይ ያመጣው ለውጥ የለም

  • አንድሩ ሃርዲንግ
  • የቢቢሲ አፍሪካ ወኪል

ባለፈው ሳምንት አንድ ምሽት ላይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ብዙ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ተሰባስበው አካባቢያቸውን እየጠበቁ ነበር።

መኪኖችን አስቁመው ይፈትሻሉ። አስፈላጊ ሰነዶችንም ይመለከታሉ።

በአዲስ አበባ በርካታ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ተሰባስበው አካባቢያቸውን ሲጠብቁ።ፍተሻውን እያስተባበሩ የነበሩት የዕድሜ ባለ ፀጋ “ሰፈራችን ውስጥ ያቋቋምነው ኮሚቴ 180 አባላት አሉት። ብዙ ሰዎችን ይዘናል። ሽጉጥ እና ፈንጂን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አጠራጣሪ ቁሳቁሶችን አግኝተናል” ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በአገር አቀፉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የትግራይ አማጺያን እና ደጋፊዎቻቸውን ነው የሚፈልጉት።

ተቺዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገቢ ባልሆነ መንገድ መታሰራቸውን ቢናገሩም፤ በመዲናዋ ግን እስሩ ሰፊ ድጋፍ ያለው ይመስላል።

ምሽት ላይ ሰፈራቸውን ይጠብቁ ከነበሩት አንዱ “ሊያመልጥ እየሞከረ ነው፤ ፍጠኑ” እያለ በስልኩ ሲነጋገር ይደመጣል።

ከእሱ በቅርብ ርቀት በብዛት አረጋውያን በጎ ፈቃደኞች ለሥልጠና ተሰብስበዋል። የሚሰጣቸውን ትዕዛት ተከትለው ይለማመዳሉ።

በመዲናዋ ያለው አጠቃላይ ድባብ ሰላማዊ ይመስላል።

ሆኖም ግን ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት በኢትዮጵያ ያለው ደኅንነት ሁኔታ “እያሽቆለቆለ” ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ማስጠንቀቂያው የተሰጠው የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ የመዝመት ፍላጎት እንዳላቸው ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።

የሩሲያ ኤምባሲ በበኩሉ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ መዲና የዕለት ተዕት ሕይወት ላይ ያመጣው ለውጥ የለም” ሲል በማኅበራዊ ገጹ አስፍሯል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መስል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ሜዳ ዘምተው ሠራዊቱን እንደሚመሩ ካሳወቁ በኋላ አፋር ግንባር ላይ ሆነውን የሚያሳይ ቪድዮ ተላልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው፣ በወታደሮች ተከበው ይታያሉ።

“አሁን አካባቢውን መቆጣጠር ችለናል። የሠራዊቱ ሞራል በጣም የሚያስደስት ነው። የኢትዮጵያ ነጻነት እስከሚረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም” ብለዋል።

በህወሓት ተይዘው የነበሩ ብዙ ከተሞችን መከላከያ እየተቆጣጠረ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በእነዚህ ውጊያ እየተካሄደባቸው ባሉ አካባቢዎች የስልክ መስመሮች ስለማይሠሩ የተባለውን ለማረጋገጥ ከባድ ነው።

በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣው አዲስ መመሪያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና የጦር ሜዳ ውጤቶችን ከተፈቀደለት አካል ውጪ ማንም እንዳይገልጽ ይከለክላል።

የህወሓት አመራሮች በቅርቡ በድሮን በተቀረጸ ቪድዮ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው ያሏቸውን ምርኮኞች አሳይተዋል። በተለያዩ ግንባሮች ወደ ፊት እየገፉ እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ዋነኛ ትኩረት የሆነችው የደብረ ብርሃን ከተማ ናት። ከተማዋ ከአዲስ አበባ ውጭ መከላከያ በከፍተኛ ተጠንቀቅ የሚገኝባት እንደሆነች ይታመናል።

አንዳንድ ተንታኞች፤ የትግራይ ኃይሎች ለመልሶ ማጥቃት እንደሚጋለጡ፣ ኤርትራም ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችልና ሠራዊቱ ከአቅሙ በላይ ውጥረት ሊገትመው እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ሰዎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ

የትኛውም ወገን እያሸነፈ ቢሆን የውጊያው መስፋፋት ሰብዓዊ ቀውሱን አባብሶታል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ እንደሚፈልጉ ገልጿል።

የድርጅቱ የአዲስ አበባ ኃላፊ ክሌር ነቪሊ “ግጭቱ በሰሜን ኢትዮጵያ መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለአስከፊ ችግር እየተጋለጡ ነው” ብለዋል።

በትግራይ አማጽያን የሚደርሰው ጥቃት፣ የፌደራል መንግሥቱ ቢሮክራሲ እንዲሁም አለመረጋጋቱ ሰብዓዊ እርዳታን እያደናቀፈ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባሉ ሁለት የአማራ ክልል ከተሞች በቅርቡ እርዳታ ማድረስ ችሏል።

ጦርነት ከ’ካህዲዎች‘ ጋር

መሪው ብልጽግና ፓርቲ በጎ ፈቃደኛ ዘማቾችን ለማመስገን ሕዝባዊ ክንውኖች አዲስ አበባ ውስጥ ማካሄዱን ቀጥሏል።

የከተማ ምክር ቤት አባሉ ኢቲሳ ደሜ “ከአገር ውስጥ አሸባሪዎች እና ከውጭ ደጋፊዎቻቸው ጋር ጦርነት ውስጥ ነን” ይላል።

የ22 ዓመቱ ባቡሽ ስጦታው “ለአገሬ ክብር እንድዋጋ ተጠርቻለሁ። ቤተሰብ ቢሞት በአገር ይለቀሳል፤ አገር ከሌለ ግን ወዴት ይደረሳል? ሕይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። ገና ሥልጠና አለመውሰዳችን አያሰጋኝም” ይላል።

አዛውንቷ ድንቅነሽ ንጋቱም ለተሰበሰበው ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“አገሬን እወዳታለሁ። መዝመት እፈልግ ነበር። ግን ባለቤቴ እና ልጄ አንቺ አትዝመቺ እኛ እንዘምትልሻለን አሉኝ።”

አዛውንቷ አክለውም “በበጎ ፈቃደኛነት ሰልጥኛለሁ። ልጄና ባለቤቴ ጦር ግንባር ሲዋጉ እኔ አካባቢዬን እጠብቃለሁ። መንገድ ላይ የማየውን ሰው ሁሉ ዝመቱ እላለሁ። ጠላት መጥቶ እስከሚገድለን መጠበቅ የለብንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች አንዷ አይዳ አወል “ጀግና ናቸው። ለሁላችሁም ተስፋ ይሆናሉ” ስትል ድንቅነሽን አቅፋ ተናግራለች።

“በርካታ ወጣቶች የእሳቸውን አርአያ እንደሚከተሉ እንጠብቃለን። የኢትዮጵያ መንፈስ ከመቼውም በላይ አሁን ጠንክሯል። ከአራዳ ክፍለ ከተማ ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች አገራቸውን ለመርዳት ለመዝመት ወስነዋል” ብላለች አይዳ።

በኢትዮጵያ ጉዳይ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ ሰዎች ይዘው የወጡት 'ከአሁን በኋላ ይበቃል' የሚል መፈክር።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ ጉዳይ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ ሰዎች ይዘው የወጡት ‘ከአሁን በኋላ ይበቃል’ የሚል መፈክር።

የ ‘ኒዮ-ኮሎኒያሊዝም’ ክስ

የኢትዮጵያ መንግሥት የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት እና መገናኛ ብዙኃን የግጭቱን እውነተኛ ገጽታ የሚያዛባ መረጃ የማሰራጨት ዘመቻ ሆነ ብለው ከፍተዋል ሲል ይከሳል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስተያየት የሚስማሙ ይመስላል። አገሪቱን ለማጣጣል እና የህወሓትን ድል ለማጋነን “ቅኝ ግዛታዊ” ሙከራ ተደርጓል ሲሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየት ይሰጣሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ አቻምየለህ እውነቱ “በሁለት ግንባሮች ጥቃት ተከፍቶብናል። አንደኛው ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎችም ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የከፈቱብን ኒዮ ኮሎኒያል የሆነ የተሳሳተ መረጃ ስርጭት ነው። ሌላው ህወሓት የከፈተው የዘር ጭፍጨፋ ጦርነት ነው” ይላል።

የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደሚተች የሚናገረው አቻምየለህ፤ ቢሆንም ግን የአገሩን ሉዓላዊነት ከመከላከል ወደኋላ እንደማይል ይገልጻል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለቃለ መጠይቅ ከቢቢሲ በተደጋጋሚ የቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለም።

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጫና በማሳደር በስፋት ይተቻል። መገናኛ ብዙኃንን የተመለከተ አደገኛ ትርክት በማስነገር እና መረጃ እንዳይገኝ በመገደብም ይኮነናል።

ከጦርነቱ በፊት የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን ከእስር በመፍታት ሲሞገሱ የበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዳግመኛ መገናኛ ብዙኃንን የሚያፍን እና የሚያስፈራራ ሁኔታ በመፍጠር እየተተቹ ነው።

ቢቢሲ በበኩሉ ስለ ኢትዮጵያ እና የተቀረው ዓለም ገለልተኛ፣ ትክክለኛ እና ወገንተኝነት የሌለው ዘገባ በማቅረብ እንደሚቀጥል ይገልጻል።