በአዲስ አበባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በኋላም የመሬት ወረራ መስፋፋቱ ተነገረ

በአዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር የለም ተብሏል

በአዲስ አበባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በኋላም የመሬት ወረራ መስፋፋቱ ተነገረReporter Amharic : ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበር ከጀመረ ወዲህ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ የመሬት ወረራ መስፋፋቱን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማው ውስጥ ምንም እንኳ የሌብትና ዝርፊያ ተግባራት ቢቀንሱም፣ የተፈጠረውን ግርግሩ በመጠቀም በግለሰብ ደረጃና በመደራጀት የመሬት ወራራ እየተካሄደ መሆኑን እንደተደረሰበት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አገር ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መሬት መውረር ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን በመግለጽ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሕወሓት ከሚፈጽመው የሽብር ተግባር ተለይቶ አይታይም ብለዋል፡፡

የከተማው የፀጥታ ኃይል በደረሰው ጥቆማ መሠረት በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ቀንዓ (ዶ/ር) ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ግለሰቦች ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን በሕገወጥ የመሬት ወረራ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ፣ በሕገወጥ መንገድ ተገንብተው የተገኙ በርካታ ቤቶችም መፍረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ በየአካባቢው የሚታዩ ሕገወጥ የመሬት ወረራዎችን እንዲያጋልጥ የጠየቁት ኃላፊው፣ የከተማ አስተዳደሩን ሰላም ለማስጠበቅና ከተማዋን የተረጋጋች ለማድረግ ሥጋት የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በመጠቆም፣ አሁን በአዲስ አበባ ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ዘመቻ በርካታ የጦር መሣሪያዎች፣ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና የኦነግ ሸኔ መታወቂያዎችና ሌሎች የተመሳሰሉ መታወቂያዎች፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ዩኒፎርሞች፣ እንዲሁም  በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተለያዩ አገሮች ሕገወጥ ገንዘቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተጀመረው የጦር መሣሪያ ባለቤትነት ምዝገባ ቁጥራቸው የበዙ ነዋሪዎች መሣሪያ እንዳስመዘገቡ የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ በኋላ በሕጋዊ መንገድም ሆነ በሕገወጥ መንገድ የተያዘ ነገር ግን ያልተመዘገበ የጦር መሣሪያ በተገኘበት እንደሚወረስ አስረድተዋል፡፡

ለስድስት ወራት በሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከጊዜያዊ መታወቂያ ውጪ ሕጉን በመተላለፍ መደበኛ መታወቂያ እንዳይሰጥ ቢገለጽም፣ የተወሰኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት መደበኛ ወይም ቋሚ መታወቂያ እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ቀንዓ (ዶ/ር)፣ በዚህ ድርጊት ላይ የተገኙ አካላት ከሦስት አስከ አሥር ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሕወሓትን ዓላማ ሊያስፈጽሙ ይችላሉ ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች፣ በብሔራቸው ምክንያት እንደተያዙ የሚወራው ከእውነት የራቀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡