የህወሓት በርካታ ምሽጎች መሰበራቸው ተገለጠ

የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የዘመቻ ጥሪ በማስተላለፍ ከማክሰኞ ጀምሮ በጦር ግንባር ተገኝተው አመራር መስጠት ከጀመሩ ወዲህ በበርካታ ግንባሮች ድል እየቀናው መሆኑን መንግስት ዐስታውቋል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በባቲ እና ከሚሴ ግንባሮች 12 የጦር መሪዎችን ጨምሮ በርካታ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰራዊት መገደላቸውን ትናንት ማሽሻውን ይፋ አድርጓል።

የአፋር ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ቢላይ አህመድ በበኩላቸው የመንግሥት ኃይላት ሰሞኑን ተደጋጋሚ ድል መቀዳጀታቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። «የጠላት የነበረው ምሽግ በሙሉ አስለቅቆ የእኛ ሠራዊት ነው ያለው። እያፈገፈጉ እየኼዱ ነው፤ ብዙ ሰው አልቋል። እንዳይወጡ እየተደረገ ነው። አሳጊታም አለ፤ በእዚህ በዞን አምስት ባሉ ቦታዎች እነሱ ያሰቡት በሙሉ እንዳይሳካ አድርጎ፤ ቆፍረው የነበረውን ምሽግ እንዳለ አስለቅቆ በአሁን ሰአት የእኛ ኃይል ነው ያለው።»የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ ትናንት «ተደመሰሱ» ያሏቸዉ የሕወሓት የጦር አዛዦች በሐገር ክሕደት ወንጀል መንግስት ሲፈልጋቸው የነበሩ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና አንቶኒዮ ጉተሬሽ እና ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለው ጦርነት እንዲያበቃ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘገበ። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የመንግሥት ኃይላት ከሕወሓት እና ተባባሪዎቹ ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ግንባር መገኘታቸውንም የዜና ምንጬ ዛሬ ባወጣው ዘገባው አረጋግጧል።