ሕገ-ወጥ ወታደራዊ ስልጠና በጫካ ውስጥ ሲሰጡ የነበሩ 10 አሰልጣኞች ተያዙ

ENA : በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ግለሰቦችን በመመልመል በጫካ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጡ የነበሩ 10 አሰልጣኞች መያዛቸውን ፖሊስ ገለጸ፡፡

በክልሉ ህዝብ ላይ ጥፋት ለመፈጸም በአሶሳ ወረዳ ገንገን ቀበሌ በጫካ ውስጥ ህገ-ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ 51 ተጠርጣሪዎች በቅርቡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በሕገ ወጥ መንገድ ስልጠና ሲሰጡ የነበሩት አሠልጣኞች ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ግለሰቦቹን በቁጥጥር የዋሉት በኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ግለሰቦቹ የሚያሰለጥኗቸውን አካላት ከአሶሳ ዞን መንጌ፣ አሶሳና ኦዳቢልድግሉ ወረዳዎች በመመልመል ሲያሰለጥኑ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ የተጀመረው የምርመራው ውጤት በፍጥነት ተጠናቆ ለህግ እንዲቀርብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ኮማንደር ነጋ ተናግረዋል።የምርመራ ውጤቱንም በየጊዜው ለሕዝቡ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በሕገ ወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን ግለሰቦች ጉዳይ በማሳወቅ ትብብሩን እንዲቀጥል ምክትል ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።