እስክንድር ነጋን የደበደቡት እስረኞች ለሕይወቱ አስጊ ናቸው ተብለው ቃሊቲ ከተቀየሩ በኃላ ከችሎት የተመለሰ እለት ወደ ቂሊንጦ ድጋሚ የተዘዋወሩ መሆናቸው ተገለጸ።

እስክንድር ነጋ ለህይወቴ አስጊ ናቸው ባላቸው እስረኞች ድብደባ እንደተፈፀመበት ጠበቃው ገለፁ
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኘው እስክንድር ነጋ ጥቅምት 11 ቀን ንጋት ላይ እንደተለመደው ከሌሎች እስረኞች ጋር ሆኖ ስፖርት በመሥራት ላይ እንዳለ በኹለት እስረኞች ድብደባ እንደተፈጸመበት ጠበቃው የሆኑት ሔኖክ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኹለቱ እስረኞች አስቀድመው ከእነእስክንድር ጋር በቂሊንጦ ታስረው የነበረ ሲሆን፣ እስክንድር ለሕይወቱ አስጊ መሆናቸውን ለማረሚያ ቤቱ አመልክቶ፣ ማረሚያ ቤቱም አደገኛ መሆናቸውን በማመን ወደ ቃሊት እስር ቤት አዛውሯቸው እንደነበር ነው ጠበቃው የገለጹት።
ጥቅምት 10/2014 እስክንድር ቀኑን ሙሉ ችሎት ውሎ በማታ ማረሚያ ቤት ከገባ በኋላ ንጋት ላይ የቀድሞ ታሳሪዎች ለምን እንደመጡ ሳይታወቅ በእሱ እና አብሮት ታስሮ በነበረው ስንታየሁ ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል። እስክንድር ከአስር ዓመታት በላይ በእስር ቤት እንዳሳለፈና ሲደበደብ ሐኪም ቤት መሔድ እንደማይፈልግ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም ግንባሩ ቆስሎና እግሩ ተጎድቶ በማረሚያ ቤቱ አንዲት ክፍል ውስጥ ተኝቶ ይገኛል ብለዋል። ስላለበት የጤና ሁኔታም ልንጠይቀው ብንሄድም ልናገኘው አልቻልንም ብለዋል።
በቀጣይ እስክንድር ነጋ የደረሰበትን ስቃይ ችሎት ቀርቦ ያስረዳል ነው ያሉት። ድብደባ በፈጸሙበት ኹለቱ ግለሰቦች ላይ ምን አይነት ርምጃ እንደተወሰደ እንደማያውቁም ጠበቃው ጨምረው ገልጸዋል። እንዲሁም ጥቅምት 10 የነበረውን ችሎት አቋርጠው የወጡት 40 የሚሆኑ የችሎቱ ታዳሚዎች በፖሊስ ተይዘው ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውም ተነግሯል።