አዲስ አበባ ማንነታቸው ለማይታወቁ ግለሰቦች በስማቸው ካርታ ተሠርቷል፤ 57,866 ሔክታር ቦታ በሕገወጦች ታጥሯል !

ከሕገወጥ መሬት ወረራ ጋር በተገናኘ በመሬት ማኔጅመንት ኃላፊዎች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ

  • ማንነታቸው ለማይታወቁ ግለሰቦች በስማቸው ካርታ ተሠርቷል
  • ለአረንጓዴ ልማት የተለየ 57,866 ሔክታር ቦታ በሕገወጦች ታጥሯል
  • በ120 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሥርቷል

ከሕገወጥ መሬት ወረራ ጋር በተገናኘ በመሬት ማኔጅመንት ኃላፊዎች ላይ ዕርምጃ ተወሰደየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሕገወጥ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን ከመሬት ማኔጅመንት እስከ ወረዳ ያሉ አመራር አካላት ላይ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች እንደተወሰደ አስታወቀ፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጥራቱ በየነ ሕገወጥ የመሬት ወረራና መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለውን የአሠራር ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ እየሠራቸው የሚገኙ ተግባራትን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ዓርብ ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከተማዋ ያላትን ስትራክቸራል ፕላን መሠረት በማድረግ የከተማዋን ልማት በሚያፋጥን መንገድ ለባለሀብቶችና ማኅበራዊ ተቋማት መሬት የሚሰጥበት አሠራር ሥርዓት እንዳለ ያስታወቁት አቶ ጥራቱ፣ ይህ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ከተማዋ ውስጥ ካለው ሰፊ የመሬት ፍላጎት አንፃር በሕገወጥ መልኩ መሬት ለመያዝ ያለው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫና በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በተነሳው ጦርነት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ትኩረት በሁለቱ ጉዳዮች ላይ መሆኑን ተከትሎ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት በከተማዋ የተለያዩ ክፍላተ ከተሞች መሬት ለመውረር ጥረት እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡

ከምርጫው አስቀድሞ፣ በምርጫው ወቅትና በመንግሥት ምሥረታው ወቅት ያለውን ጉዳይ የሚከታተተል የአመራር ቡድን ተዋቅሮ እንደነበር የጠቀሱ ሲሆን፣ በዚህም ሦስት ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የማጣራት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የከተማው አስተዳደር ያወጣውን መመሪያ ቁጥር 20/2013 ተከትሎ፣ መሬት ለግል ጥቅም በሕገወጥ መንገድ ለመውረር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በተመለከተ፣ በአረንጓዴ ልማት ቦታነት የሚታወቁ ቦታዎች በሕገወጥ መንገድ ታጥረው የተያዙበትን ሁኔታ፣ እንዲሁም  በከተማው ውስጥ የሚሠሩ መሠረተ ልማቶችን ምክንያት በማድረግ ለሚነሱ ተነሺዎች በምትክነት የሚሰጥ ቦታን ሌሎች አካላት በሕገወጥ  አሠራር እንዲካተቱ በማድረግ፣ መሬት በሕገወጥ መንገድ የሚተላለፍ መሆኑን ቡድኑ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በዝርዝር በተጠቀሱት የማጣራት ሒደቶች ከተከናወኑ በኋላ፣ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ሒደቱ የተሳተፉ አካላትን የመለየት ሥራ እንደተሠራ የተናገሩት አቶ ጥራቱ፣ በዚህም ሕገወጥ ድርጊቱ ውስጥ በተሳተፉ አካላት ላይ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከተወሰዱት ዕርምጃዎች መካከል የከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮች ከቢሮ ኃላፊ ጀምሮ በየደረጃው ያለው ሁሉም አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲሆን፣ ዝርዝር መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ደግሞ ለፍትሕ አካላት ተጨማሪ በወንጀል የተሳተፉት የሚጠይቁበት ሒደት ቀጥሏል፡፡

በተመሳሳይ በክፍለ ከተማ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮች፣ የአርሶ አደሩን መብትና ጥቅም ሽፋን በማድረግ መብቱ ለማይገባቸው አካላት መሬት እንዲተላለፍ ካርታ የሠሩ፣ መታወቂያ ያዘጋጁና በሕገወጥነቱ ላይ ተባባሪ የሆኑትን ከክፍለ ከተማ አመራር ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡

በ2013 ዓ.ም. በከተማ አስተዳሩ በወጣው መመርያ መሠረት አርሶ አደሮች በመሬታቸው ላይ ገቢ የሌላቸውና ከእነሱ ጋር አብረዋቸው ለሚኖሩ ልጆቻቸው እስከ 150 ካሬ ሜትር ቦታ ለቤት መሥሪያ የሚሰጡበት አሠራር እንደተቀመጠ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን መመርያ ተከትሎ በመኖሪያ ቤትነት ከአርሶ አደር ይዞታ ካርታ ወጥቶ የተሰጠባቸው ፋይሎች ተጣርተዋል፡፡

2,170 የሚሆኑ የአርሶ አደር ይዞታ የነበሩ ካርታዎች ተጣርተው፣ ከዚህ ውስጥ 497 የሚሆኑት ይዞታዎች በሕገወጥ መንገድ ለግለሰቦች የተላለፉ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም በካሬ ሲሰላ 20.7 ሔክታር መሬት እንደሆነና ይህ ተግባር የታየባቸውም ክፍላተ ከተሞች አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ፣ ቦሌ፣ ለሚ ኩራና የካ እንደሆኑ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደር ላልሆኑ ግለሰቦች መታወቂያ እንዲወጣ በማድረግና ካርታ በማሠራት እንዲተላለፍ የተደረገበት፣ በአዲስ አበባና በዙሪያ ባሉ ከተሞች የማይኖሩና ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ካርታ በስማቸው እንዲወጣ ማድረግና በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያየ መንገድ ወደ ሌላ አካል የማስተላለፍ ተግባራት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

በ2013 ዓ.ም. መግቢያ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከ1,000 ሺሕ ሔክታር በላይ የሚሆን መሬት በሕገወጥ መንገድ መያዙን ተከትሎ ወደ መሬት ባንክ እንደገባ የተናገሩት  አቶ ጥራቱ፣ ከዚህ ውስጥ 383.32 ሔክታር መሬት በድጋሚ በሕገወጥ በግለሰቦች መወረሩ በማጣራት ሥራው ማረጋገጥ ተችሏል።

ለአረንጓዴ ልማት ከተለዩ 252 ቦታዎች ውስጥ ደግሞ 35 የሚሆኑ ቦታዎች ወይም 57,866 ካሬ የሚሆን ቦታ በሕገወጥ በግለሰቦች መታጠራቸውና ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ በሠራው የማጣራት ሥራ ወደ ባንክ እንዲገባ ማድረጉን 120 ግለሰቦች ላይ ክስ የመመሥረት ሥራ መከናወኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።