በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ በህብረቱ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው – አፍሪካ ህብረት

የአፍሪካ ህብረት ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ ይመጣሉ የሚል ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው አስታወቀ።

አፍሪካ ህብረት ይህን ያስታወቀው ፥ በህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶየ በኩል ነው።

ኮሚሽነሩ ለአል-ዐይን ኒውስ በሰጡት ቃል ፥ ” በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ በህብረቱ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ” ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ከመጀመርያው አንስቶ ግጭቱን በትኩረት ሲከታተለው የነበረ ጉዳይ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ የግጭቱን መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት “በቅርቡ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ተደርገው መሾማቸው” ህብረቱ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ህብረቱ በከፍተኛ ተወካዩ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየመከረ መሆኑንም አሳውቀዋል።

እስካሁን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች መሰረት “ሁሉም የግጭቱ ተዋናዮች በመጨረሻ ወደ ጠረጴዛ እንደሚመጡ ትልቅ ተስፋ አለን” ሲሉም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት እንዲፈታ በሶስት ቁልፍ ጉዳዮች እየመከረና በግጭቱ እየተሳተፉ ካሉ ኃይሎች ጋር እየተወያየ አንደሆነ ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

“ግጭቱን ማቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር ማድረግ እና ዘላቂ የሆነ ፖለቲካ መፍትሄ ማባጀት” የሚሉ ዓበይት ነጥቦች ህብረቱ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት እንዲቆም በተደጋጋሚ እና በቀጣይነት እየሰራባቸው የሚገኙ ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ነው ኮሚሽነሩ የገለፁት።

አል ዐይን ኒውስ