ቦረና ዞን ከባድ ድርቅ ተከሰተ !

የቦረና ዞን ነዋሪዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ለውሀ፣ ለምግብና ለጤና ችግር ተጋልጠዋል።

የቦረና ዞን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬባ ኦዳ ለኤፍ ቢ ሲ በሰጡት ቃል፤ በዞኑ በ2013 ዓ.ም የበልግ ዝናብ በቂ አለመሆኑና የ2014 ዓ.ም የመኸር ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።

በደረሰው ድርቅ 539 ሺህ 679 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የውሀ እጥረት እንዳጋጠማቸው የገለፁት ኃላፊው ከዚህ ውስጥ 177 ሺህ 553 ለሚሆኑት ብቻ በቦቴ ውሀ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

እስካሁን በደረሰው የምግብ እጥረትም 6 ሺህ 398 ህፃናት ፣9 ሺህ 78 እናቶችና 2 ሺህ 226 አዛውንቶች ላይ የጤና ችግር መታየቱ ገልፀዋል።

እስካሁንም ለ118 ሺ 864 ሰዎች የምግብ እርዳታ የተደረገ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው 166 ሺህ 136 የሚሆኑት ደግሞ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አንስተዋል።

በተከሰተው ድርቅም 7 ሺህ 540 ከብቶች የሞቱ ሲሆን ÷13 ሺህ 641 የሚሆኑት ደግሞ በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ተገልጿል።

እንስሳቶቹን ከአደጋው ለማትረፍም 2 ሚሊየን 463 ሺህ 214 ቤል ሳር ከመንግስት የተጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የደረሰ ነገር እንደሌለ ተነስቷል።

አሁን ላይ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች እንደቀጠሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አንፃር ግን በቂ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡ ተዘግቧል።

ምንጭ  = ኤፍ ቢ ሲ