የአዲሱ 11ኛው ክልል ሕገመንግስትም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ከተጠናቀቁ የቆዩ ሲሆን የሚጠበቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማፅደቅ ብቻ ነው

የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች መስከረም 20/2014 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ሰጥተዋል።

ይህንን ተከትሎም የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረቱን በከፍተኛ ድምጽ መደገፋቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በዚህ ውጤት መሰረትም አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን በመደገፋቸው ለኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስራ አንደኛው ክልል ይቋቋማል።

በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል የሚሆኑት አምስቱ ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በየምክር ቤቶቻቸው ተወያይተው ከወሰኑ በኋላ በአንድነት ክልል ለመመስረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ያቀረቡት መስከረም 19/2012 ዓ.ም ነበር።

ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምስረታ በየምክር ቤቶቻቸው ተቀባይነት ያገኙ ነጥቦች ሕዝቦቹ ባላቸው ሥነልቦናዊ አንድነት፣ በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባህላዊ እሴቶች እና በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ መቀራረባቸው ነበር።

በ1983 ዓ.ም የፌደራላዊ የአስተዳደር ሥርዓቱ ከተዋቀረ በኋላ ለበርካታ ዓመታት የዘለቁት በዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በ2012 ዓ.ም የሲዳማ ክልል በሕዝበ ውሳኔ እራሱን ሲችል ወደ 10 ከፍ ማለቱ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ እዚያው ደቡብ ክልል ውስጥ የተደረገውን የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ተከትሎ አንድ ተጨማሪ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል ሊሆን ነው።

የ11ኛው ክልል የተፈጥሮ ሀብቶች

አቶ ምትኩ በድሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 39ሺህ 64ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት እንዳለው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የክልሉ ሕዝብ በዋናነት በጥምር ግብርና የሚተዳደሩ ሲሆን በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩም እንዳሉ አቶ ምትኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን አዲስ ክልል በምሥራቅ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በሰሜን የኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ የጋምቤላ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን ያዋስኑታል።

በክልሉ እንደ ጨበራ ጩር ጩራ እና ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ።

በዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል የሚገኘው እና ከ29 የሚበልጥ አጥቢ የዱር እንስሳትን በውስጡ የያዘዉ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የአገር ጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

በፓርኩ ዝርያው እየተመናመነ የመጣዉ የአፍሪካ የዝሆን፣ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና እንደ አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት ይገኛሉ።

በዚሁ ክልል ከሚገኙ የተፈጥሮ መስህቦች መካከል አንዱ የንጉሥ ሃላላ የድንጋይ ካብ አንዱ ሲሆን መገኛውም ዳውሮ ዞን ነው።

የሃላላ ካብ ከ175 ኪ.ሜትር በላይ ርዝመት ያለውና አሰራሩ አስገራሚ የሆነዉ የድንጋይ ካብ የዚሁ ክልል የቱሪስት መስህብ ነው።

በገበታ ለአገር ከሚለሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ኮይሻ ፕሮጀክት የሚገኘው የዚሁ አዲስ ክልል አካል በሆነው በኮንታ ልዩ ወረዳ ነው።

በተጨማሪም በሸካ ዞን የሚገኘው ጥብቅ ደን፣ የከፋ የጫካ ቡና እንዲሁም ሰፊ ሽፋን ያለው ደን የዚሁ ክልል አካላት ናቸው።

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በዚሁ ክልል የሚገኝ ሲሆን በውስጡም ልዩ ልዩ የዱር እንሰሳትና ዕፅዋት ይገኙበታል።

75 አጥቢ እንስሳትንና 325 የአዕዋፍ ዓይነቶችን እንደያዘ የሚነገረው ይህ ብሔራዊ ፓርክ፣ ውድንቢዎች፣ የመጋላ ቆርኪ መንጋ፣ ሳላዎች፣ የሜዳ ፍየሎች እና ሌሎም አጥቢዎች ይገኛሉ።

ውድንቢ በኢትዮጵያ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ የዱር እንሰሳ ነው።

በክልሉ በሰፊው እንደሚገኝ የሚነገረው የብረት እና የድንጋይ ከስል ማዕድናትን ተከትሎ በዳውሮ እና ኮንታ አካባቢዎች ፋብሪካዎች እየተገነቡ መሆኑን አቶ ምትኩ ተናግረዋል።

ሕገ መንግሥት

በዚህ ክልል በ2014 ዓ.ም 3̂.6 ሚሊዮን ሕዝብ ገደማ ይኖርበታል ተብሎ እንደሚገመት አቶ ምትኩ ይናገራሉ።

በክልሉ 13 ነባር ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመምጣት ተቀላቅለው የሚኖሩ ሕዝቦችም ይገኙበታል።

ከሕግ ባለሙያዎች፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 12 ባለሙያዎች የክልሉን ሕገ መንግሥት በማርቀቅ መሳተፋቸውን አቶ ምትኩ ይናገራሉ።

በዚህ የክልሉ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ይሆናል ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ በየእርከኑ ያሉ አካላት ደግሞ የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ እንዲወስኑ ይደነግጋል።

በክልሉ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመያዝ የከፋ ዞን ቀዳሚ ሲሆን፣ በዞኑም ከፊኛ ይነገራል።

በክልሉ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነው የዳውሮ ዞን ሲሆን ዳውሮኛ ደግሞ ቋንቋው ነው።

በቤንች ሸኮ አራት የሚሆኑ ብሔረሰቦች የሚገኙ ሲሆን ሁሉም የየራሳቸው ቋንቋ አላቸው።

ሸካም እንደዚሁ ሦስት፣ ምዕራብ ኦሞም አራት ብሔረሰቦች ይኖሩበታል።

በተጨማሪም ኮንታ ልዩ ወረዳ የራሱ የሆነ ቋንቋ አለው።

በክልሉ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ላይ የክልሉ ስያሜ ይሆናል ተብሎ የተቀመጠው ‘የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች’ መሆኑን አቶ ምትኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የክልሉ ሰንደቅ ዓላማንም በተመለከተ ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ገጽታ፣ የሕዝቡን ባህል እና ታሪክ ያገናዘበ እንዲሁም ሌሎች እሴቶችን ያካተተ ረቂቅ ሰንደቅ ዓላማ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡም ተገልጿል።

የክልሉ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የክልሉ መንግሥት ምስረታ ዕለት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ምትኩ፣ ይህም ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለማድረግ ታስቧል።

ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ውጤትን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔውን ማጽደቅ እንደሚጠበቅበት፣ ከዚያ በመቀጠል የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሥልጣን ርክክብ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ምስረታ በዕቅድ ደረጃ ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም ተብሎ የተያዘ ቢሆንም በእነዚህ ተቋማት የጊዜ ሰሌዳ እና ውሳኔ መሰረት የሚወሰን መሆኑን ያብራራሉ።

የክልሉ መንግሥት መቀመጫዎች

11ኛውን ክልል ለመመስረት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ በደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ስር በነበሩበት ወቅት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት እስከ 1000 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ ይጠይቃቸው እንደነበር አቶ ምትኩ ያስታውሳሉ።

ይህም ለተለያዩ እንግልቶች መዳረግ ብቻ ሳይሆን የልማት ኢፍትሃዊነት ጭምር ማስከተሉን አክለው ገልፀዋል።

ከዚህም በመነሳት አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የክልሉ መንግሥት መቀመጫ እንዲሆን ያሰባቸው ከአንድ በላይ ከተሞች መሆናቸውን አቶ ምትኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጉዳዩ ገና በጥናት ላይ ያለ እና ያልተጠናቀቀ ነው በማለት ተጨማሪ ነገር ከመዘርዘር የታቀቡት አቶ ምትኩ፣ የክልሉ መንግሥት ከአንድ ከተማ በላይ እንዲኖሩ በማድረግ ክልሉን እንደሚያስተዳድር በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ መቀመጡን ግን ተናግረዋል።

ይህም አገልግሎትን እና መሰረተ ልማቶችን ለሕዝቦች ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ እየተጠና መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

“አዲሱ ክልል በኢትዮጵያ ያልተለመደ የማዕከላትን አሰራር እየተከተለ ነው” በማለት ይህንን ልምድ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከታንዛኒያ፣ ከቤኒን እና ከኮትዲቯር መውሰዳቸውን ይናገራሉ።