የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ነጥብ ይፋ ሆነ

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ነጥብ ይፋ ሆነ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን የ2011 ዓ.ም የመግቢያ ነጥብ ይፋ አደረገ።

ቢሮው በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የአገሪቱን ዕድገትና የገበያ ሁኔታ መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎችን ለመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አንዱአለም ዘውዴ ይህንን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ትስስር የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ተማሪዎች በሚፈልጉት የትምህርት ዘርፍ በመንግስትና በግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ማዕከላት መማር ይችላሉ ብለዋል።

የመግቢያ ነጥቡ በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት እኩል መሆኑንና በግል መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች የሚማሩበት ተቋም እውቅናና የ2011 ዓ.ም የምዝገባ ፍቃድ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ይህንንም በቢሮውና በየወረዳው ባሉት የቢሮው ጽህፈት ቤቶች በመሄድ ወይም የቢሮውን የፌስቡክ ገጽ በመጎብኘት ማጣራት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የመግቢያ ነጥቦቹም 10ኛ ክፍል ላጠናቀቁ ለደረጃ አንድ ለወንዶች 1 ነጥብ 7 እና ከዚያ በታች፣ ለሴቶች 1 ነጥብ 56 እና ከዚያ በታች፤ ለደረጃ ሁለት ከ1 ነጥብ 71 እስከ 2 ነጥብ ለወንዶች እና ለሴቶች ከ1 ነጥብ 57 እስከ 1 ነጥብ 86 ነው።

ለደረጃ ሶስት ለወንዶች ከ2 ነጥብ 14 እስከ 2 ነጥብ 41 እና ለሴቶች ከ2 ነጥብ እስከ 2 ነጥብ 15፣ ለደረጃ አራት ለወንዶች ከ2 ነጥብ 42 እስከ 2 ነጥብ 7 እና ለሴቶች ከ 2 ነጥብ 16 እስከ 2 ነጥብ 56፣ ለደረጃ አምስት ለወንዶች 2 ነጥብ 71 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴቶች 2 ነጥብ 57 እና ከዚያ በላይ የመግቢያ ነጥብ መሆኑ ታውቋል።

የ12 ክፍል ላጠናቀቁ ተማሪዎች የመግቢያ ነጥብ ለደረጃ ሶስት ለወንዶች 268 እና ከዚያ በታች ለሴቶች ደግሞ 265 እና ከዚያ በታች፤ ለደረጃ አራት ለወንዶች ከ269 እስከ 290 እና ለሴቶች ከ266 እስከ 285፤ እንዲሁም ለደረጃ አምስት ለወንዶች 291 እና ከዚያ በላይ ለሴቶች 286 እና ከዚያ በላይ መሆኑ ተገልጿል።

የ2011ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው በቴክኒክና ሙያ ለመሰልጠን ለሚፈልጉ ሰልጣኞች በደረጃ አምስት በመረጡት ሙያ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
በዲግሪ ወይም በማስተርስ የተመረቁ ሆነው ቴክኒክና ሙያ ለመሰልጠን የሚፈልጉ ምሩቃን በደረጃ 4 እና 5 ተመዝግበው ስልጠና መውሰድ እንደሚችሉም ተብራርቷል።

ማንኛውም የዕውቅና ፍቃድ የተሰጠው ኮሌጅ የእውቅና እና የምዝገባ ፍቃድ ደብዳቤ ለተመዝጋቢዎች ግልጽ በሆነ ቦታ ኮፒውን በመለጠፍ እንዲያውቁት ማድረግ ይኖርበታል ነው ያሉት አቶ አንዱአለም።

ኮሌጆች ሰልጣኞችን መመዝገብ የሚችሉት ዕውቅና ፍቃድ በተሰጣቸው ካምፓስ፣ ደረጃ እና የሙያ ዓይነት ብቻ ነውም ብለዋል።

ኮሌጆች በ2011 ዓ.ም የሚቀበሏቸውን ሰልጣኞች የሚመዘግቡት በ2011 ዓ.ም በወጣው መግቢያ ነጥብና መስፈርት ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቢሮው በ2010 ዓ.ም እውቅና ሳይኖራቸውና ከጥራት በታች የሚያሰለጥኑ 22 ኮሌጆችን እውቅና መሰረዙንም ገልጸዋል።