በቤኒሻንጉል በተደራጀ መልኩ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ የጥፋት ሃይሎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ ፀረ ሰላም ሃይሎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ ፀረ ሰላም ሃይሎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ወረዳ ገንገን ቀበሌ ልዩ ቦታዉ ዛለን ወንዝ በሚባል ስፍራ በተደራጀ መልኩ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ በነበሩ የጥፋት ሃይሎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን ለኢቢሲ እንደተናገሩት ህዝቡ ባደረሰን መረጃ መሰረት ቁጥራቸዉ በአሶሳ ወረዳ ገንገን ቀበሌ ልዩ ቦታዉ ዛለን ወንዝ በሚባል ስፍራ በተደራጀ መልኩ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የጥፋት ሃይሎች ላይ የክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊስ እርምጃ ወስዷል፡፡

በተደረገዉ ወታደራዊ ኦፕሬሽን 31 የሚሆኑ የጥፋት ሃይሎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ከ1 መቶ በላይ የሚሆኑ የሰልጣኝ ቤቶች እንዲወድሙ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከ20 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በፈቃደኝነት እጃቸዉን መስጠታቸዉንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ሲሰለጥኑበት የነበረ አንድ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከተያዙት ሰልጣኞች በተገኘዉ መረጃ መሰረት ለጊዜዉ በተሰወሩ የጥፋት ሃይሎች ጋር ከ12 በላይ የሚገመት የጦር መሳሪያ አብሮ እንደተሰወረ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

ስልጠናዉን የሚወስዱት በተደራጀ ካምፕ ዉስጥ የነበረ ሲሆን የህክምናና የምግብ አገልግሎት በተሟላ መልኩ ይቀርብ እንደነበር መታወቁን የገለፁት ኮሚሽነሩ ልዩ ሃይሉ በወሰደዉ እርምጃ ካምፑን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ተችሏል ብለዋል፡፡

የጥፋት ሃይሎች ዓላማ የክልሉን ሰላም ማደፍረስና የተለያዩ የጥፋት አጀንዳዎችን በማንገብ ህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ለኮሚሽኑ በደረሰዉ መረጃ መሰረት ከ4 መቶ በላይ የሚሆኑ የጥፋት ሃይሎች በተደራጀ መልኩ ከ 1 ወር በላይ ህገ ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ እንደነበር ታዉቋል ብለዋል፡፡

ሸሽተዉ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ገቡትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የኦፕሬሽን ስራዉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ የጥፋት ሃይል ሰልጣኞች 10 ዓመት ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ታዳጊና ጎልማሶች ናቸዉ፡፡ በጥፋት ሃይሎች ወታደራዊ ስልጠና ዉስጥ ከመመልመል አንስቶ እስከ የጦር ትጥቅና የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ አካላት የመለየት ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

አኩራፊ ሃይሎች እና አፈንጋጭ የቤህነን ወታደሮች እንዳሉበት ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነሩ የምርመራ ሂደቱን በቀጣይ ለህዝቡ የምናሳዉቅ ይሆናል ብለዋል፡፡