ሀገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ምን ይደረግ? – ቴወድሮስ ኅይለማርያም (ዶ/ር)

ሀገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ምን ይደረግ?
***
ቴወድሮስ ኅይለማርያም (ዶ/ር)
***
መግቢያ
***
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ በዓይነታቸውም ሆነ በመጠናቸው ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁና ታላቅ ብሔራዊ ቀውስ የሚያስከትሉ የእርስ በርስ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው እንዲባረሩ፣ ቤትና ንብረታቸው እንዲዘረፍና እንዲወድም፣ ሕይወታቸውን በበጎ አድራጎትና በጊዜያዊ መጠለያዎች በአሳሳቢ ሁኔታ እንዲገፉ አስገድደዋል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈው ተገድለዋል ተቃጥለዋል፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ4 ዓመት ሕፃናት ጀምሮ እስከ 80 ዓመት አዛውንት ሴቶች ተገድደው ተደፍረዋል፡፡ መጠኑ የማይታወቅ የትየለሌ የሀገር ሀብት በአመፅ ወድሟል፡፡

በቅርቡ የወጣው ዓለም ዐቀፍ ዘገባ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ በውስጣዊ መፈናቀል መጠን ከዓለም የአንደኛነቱን ደረጃ ይዛለች፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመው ሀገሮች በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ወዲህ ያለውን ተጨባጭ የግጭት ካርታ ብናስተውል ቀድሞ በአብዛኛው በጠረፋማ ክልሎች ተወስኖ የነበረው ማንነት ተኮር ግጭትና መፈናቀል ቀስ በቀስ ወደ መሃል አገር እየዘለቀ እስከ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ደጃፍ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የትኛውም ክልል ከአመፅና ከአሳሳቢ የግጭት ስጋት ውጭ ባለመሆኑ ችግሩ ወደ ብሔራዊ ቀውስነት አድጓል፡፡ ያለንበት የአፍሪካ ቀንድ በዓለማችን ግንባር ቀደም የግጭት ቀጠና መሆኑ ግምት ውስጥ ሲገባ ታላቅ አደጋ እንደተደቀነብን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

እንዴት እዚህ አዘቅት ውስጥ ልንወድቅ በቃን? ከእንግዲህስ ከተደቀነብን ብሔራዊ የመበታተንና የእልቂት አደጋ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት? እነዚህን ጥያቄዎች በመጠኑ ለመዳሰስ የዘውጋዊ ግጭቶችን መሠረታዊና የቅርብ መንስኤዎችና ባሕርያት መለየት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ረገድ ዘውገኝነት የብሔራዊ ህልውናችን አልፋና ኦሜጋ የሆነበትን የዘመነ ኢሕአዴግ ታሪካዊ ሂደት ስንመረምር የሥርዓቱ ፈጣሪና ዘዋሪ ከሆነው ከኢሕአዴግ የፖለቲካ እጣፈንታ ጋር የተቆራኙ ሁለት ዐበይት የግጭት እርከኖች እናገኛለን፡፡

ኢሕአዴግና የግጭት ህልውናው
***
በታሪካችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ዜጎች በብሔረሰባዊ ማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ መገለልና ጥቃት የደረሰባቸው በዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕወሓት/ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጠባቸው 26 ዓመታት ጠብጫሪ ዘውጋዊነት ሰፊ ርዕዮታዊ፣ ሕጋዊና መዋቅራዊ መሠረት የጣለበት የመጀመሪያው እርከን ነው፡፡ በዚህ ወቅት መንግሥት በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር የተሳተፈባቸው ዘውግ ተኮር ጥቃቶች ዋነኛ ዒላማ የአማራ ሕዝብ ቢሆንም ፣ ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች የጎሳ ግጭቶች ቀጥተኛ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በአማካይ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን በማንነታቸው ምክንያት የዜግነት መብቶቻቸውን በመግፈፍ ለሕጋዊና መዋቅራዊ መድልዎ ዳርጓቸዋል፡፡ በገዛ ሀገራቸው በ‹‹ስደተኝነት›› ተፈርጀው በማንኛውም ወቅት ለዘር ጥቃት እንዲጋለጡና ሕይወታቸውን በስጋት እንዲገፉ ፈርዶባቸዋል፡፡

በርካታ ምሁራንና የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚጠቁሙት ኢሕአዴግ የንዑስ ዘውግ አገዛዝ በመሆኑ ህልውናው በግጭት አስተዳደር ላይ ጥገኛ ነው፡፡ በከፋፍለህ ግዛው መርህ በማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ስንጥቆችንና ልዩነቶችን በማራገብ የሚጠቀም፣ ከሀገር በቀልነት ይልቅ የቅኝ አገዛዝ ዝንባሌ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የፈጠረው ፌዴራላዊ ሥርዓት ጎሰኝነትን በተግባር ብቸኛው የፖለቲካ መደራጃና የቁሳዊና ትዕምርታዊ ጥቅማጥቅሞች ማግኛ መንገድ ያደረገ ነው፡፡

ብሔራዊ ፖለቲካውና መንግሥታዊ መዋቅሩ የሀገሪቱን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ግምት ውስጥ ያላስገባና ለአንድ ቡድን የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የተጫነ ነው፡፡ ማንነታዊ ግጭቶችን ከምንጫቸው ከመከላከልና በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ ከማዕከላዊው መንግሥት ጫንቃ ላይ አውርዶ በክልላዊና ዘውጋዊ ደረጃዎች ለመገደብ የታለመ ነው፡፡ ከብዝሃ ባህላዊነት መርሆች እጅግ ያፈነገጠና በአብሮነትና መቻቻል ፈንታ መቃቃርንና አጉል ፉክክርን የሚያበረታታ፣ በይነ ዘውጋዊ ድልድዮችን በማፍረስ የልዩነት ግንቦችን የሚገነባ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ሥርዓት በአስተዳደራዊ ወሰኖችና ግዛት ይገባኛል ምክንያት ከግጭትና ከውጥረት ነፃ የሆኑ ክልሎች የሉም፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ ባሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦችም ጭምር እያደር ከሚፈነዱ ማንነታዊ ግጭቶች አልዳኑም፡፡ ለምሳሌ 58 ብሔረሰቦችን በአንድ ላይ ጨፍልቆ የተቋቋመው የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ውስብስብ የጎሳ ፖለቲካ ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ የተቀበረበት ክልል ነው፡፡ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ይልቅ በየብሔረሰቡ ስም የተፋጠጡ ልሂቃን የፈሉበትና ለማህበራዊ ሽብር ሴራ የተመቻቸ ነው፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው አክራሪ ጎሰኝነትን የሚሸልም ሥርዓት ነው፡፡ በአገዛዙ የፊት ተርታ የተሰየሙ ቁንጮ ሹማምንትንና ቡድኖች በብሔረሰቦች መካከል ንቀትና መጠራጠርን የሚዘሩ፣ ጥላቻ የተቀቡ ሐሳቦችን በአደባባይ ያለሃፍረት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ከበደኖ እስከጉራ ፈርዳ፣ ከመተከል እስከ ኦጋዴን ሚሊዮኖችን ያፈናቀሉ፣ የዘረፉና ያዘረፉ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን የገደሉና ያስገደሉ ግለሰቦች በሀገር መሪነት የተሰየሙበት ሥርዓት ነው፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ኢሕአዴግ በማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ልማዳዊ ግጭቶች ግብታዊና አካባቢያዊ ባሕርያቸውን እየለቀቁ በሕግና በመዋቅር ወደተደራጁ መደበኛ ዘውጋዊ ግጭቶች አድገዋል፡፡ በማንነት ጥያቄ፣ በዞንና በክልል ጥያቄ፣ በምጣኔ ሀብት ክፍፍልና በሥልጣን ድልድል፣ በትዕምርታዊ ባለቤትነት ጉዳዮች፣ ወዘተርፈ ወንድማማች ማኅበረሰቦችን በባላንጣነት ያሰለፉ ውጥረቶችና ግጭቶች በመላ ሀገሪቱ ያለማሰለስ ተቀስቅሰዋል፡፡ ነገር ግን የሥርዓቱ አምበል የሆነው ሕወሓት/ኢሕአዴግ በሥልጣን እስከቆየ ድረስ ግጭቶች በታችኞቹ የአስተዳደር እርከኖች እንዲገደቡና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ በስልት የተያዙ ነበሩ፡፡

የተደራጀ ሽብርና ዘር ማፅዳት
***
ሁለተኛው የግጭት እርከን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢሕአዴግ አገዛዝ ላይ ከተነሳው ሰፊ ሕዝባዊ አመፅ ጋር የተቆራኘውና በሀገሪቱ የሚከሰቱ የዘውጋዊ ግጭቶች ባሕርይ፣ የተዋናዮች ሚና ፣ የግጭቱ አድማስና የጉዳት ደረጃው ታላቅ እመርታ ያሳየበት ወቅት ነው፡፡ ይህ እርከን ከኢሕአዴግ ማዕከላዊነት ወደዳር የተገፋውና የበላይነቱን የተነጠቀው ወያኔ – ሕወሓትና ግብረ አበሮቹ ህልውናቸውን ለማስጠበቅና በሀገሪቱ የተነሳውን የለውጥ ማዕበል ለመቀልበስ፣ ለ26 ዓመታት የተዘረጋውን የግጭት ሥርዓት በማንቀሳቀስ የሞት ሽረት ፍልሚያ የሚያደርጉበት ነው፡፡
በተለይ ከአንድ ዓመት ወዲህ የተከሰቱትና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ሦስት ዐበይት ክስተቶች በሀገሪቱ ህልውና ላይ ያንዥበበው አደጋ ሁነኛ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ከሶማሌ ክልል ወደ 1 ሚሊዮን ኦሮሞዎችና ከኦሮሚያ ከ100 ሺሕ በላይ ሶማሌዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ወደ 800 ሺሕ የሚጠጉ ጌድኦዎች ከኦሮሚያ ክልል በግፍ ተባርረዋል፡፡ ከሳምንት በፊት በቤንሻንጉል ክልል በተቀሰቀሰውና እስካሁንም በቀጠለው የዘር ጥቃት ወደ 100 ሺሕ ኦሮሞዎችና አማሮች ተፈናቅለው ሰብአዊ እርዳታ እንኳን ለማግኘት በማይችሉበት አስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ እንጂ በመላ ሀገሪቱ ማቆሚያ የሌላቸው ግጭቶች ተበራክተዋል፡፡ እስካሁንም መፍትሔ ያጣው የጉጂና የጌድኦ፣ የጉጂና የቡርጂ፣ የኮሬና የቡርጂን ብሔረሰቦች ያካተተው የእርስበርስ ውጊያ ወራትን አስቆጥሯል፡፡ በከፋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ ወዘተ. አዳዲስና ነባር የብሔረሰብ ግጭቶች ከፍተኛ ሰብአዊ ሰቆቃ ማስከተል ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የዘር ጥቃቶችና ግጭቶች አድማሳቸውን ወደ ትላልቅ ከተሞችና ወደ ማዕከል እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በሐዋሳ በፊቼ ጫምባላላ አከባበር በሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው መጠነ ሰፊ ግጭት ወልቂጤና ወላይታን ጨምሮ በበርካታ ሥፍራዎች ተዛምቷል፡፡

በተመሳሳይ መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የኦነግን አቀባበል ታክኮ የተከሰተው ግጭት ጉዳዩ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በፍጥነት እየተስፋፉ የሚገኙት የእርስ በርስ ግጭቶችና ሰብአዊ ቀውሶች የተጠኑ፣ የታቀዱ፣ የተደራጁ፣ በመንግሥታዊ አካላት የሚደገፉ፣ የመንግሥት ሀብትና ኀይልን የሚጠቀሙ የዘር ማፅዳት ድርጊቶች ናቸው፡፡ ሀገሪቱ የምትገኝበት ሥርዓታዊ ሽግግር በመንግሥት አቅምና ችሎታ ላይ ያስከተለውን ክፍተት በመጠቀም በአዲሱ ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸውና ነባር አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የተነሳሱ ቡድኖች በነጠላና በቅንጅት የሚያቀጣጥሏቸው አመፅና ግጭቶች ናቸው፡፡
በኦጋዴን የተሰሩት አሰቃቂ ግፎች በክልሉ ልዩ ኀይሎችና ‹‹ሄጎ›› በሚባሉ የሰለጠኑ ወጣት የሽብር ሚሊሻዎች የተከናወኑ ናቸው፡፡ በሐዋሳም የግጭቱ ቀስቃሶችና መሪዎች በብላቴ ወታደራዊ ካምፕ ለአንድ ወር ያህል ሥልጠና የተሰጣቸውና በአምስት የሽብር ብርጌዶች የተደራጁ ቦዘኔዎችና በረንዳ አዳሪዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ እንዲህ ያሉ ግዙፍ የጥፋት እቅዶችን የሚነድፍና ከሠራዊት ምልመላወና ሥልጠናው እስከደም ድርጎው የሚፈልገውን በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት በጀት የሚሸፍን ኀይል መኖሩ አያጠራጥርም፡፡

በዋነኝነት በየአቅጣጫው የሚለኮሱት የሽብር ድርጊቶችና የዘር ማፅዳት ዘመቻዎች መሪ ተዋናዮች የኢሕአዴግ የጎሳና የዝርፊያ ፖለቲካ ያፈራቸውና ለውጡ የመጣባቸው ልሂቃን ናቸው ነው፡፡ ከገዛ ጥቅማቸው ውጭ የማይታያቸው፣ ሰላምና መረጋጋትን የማይሹ፣ በሕዝቦች መካከል ደመነፍሳዊ ጥላቻን፣ ፍራቻን፣ ጥርጣሬንና ምቀኝነትን በማራገብ ለእኩይ ዓላማቸው የሚያሰልፉ የጎሳ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ግባቸውም ዙሪያ ገብ ቀውስ በመፍጠር የለውጡን ሂደት መቀልበስ፣ አዲሱን መንግሥት አፍርሶ ሥልጣንን መልሶ መጨበጥ ነው፡፡ ይህ ካልተሳካ ደግሞ አገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በርስ ደም መፋሰስ መክተት ነው፡፡

ከገባንበት አዘቅት እንዴት እንውጣ ?
***
ከላይ በአጭሩ ለማሳየት እንደተሞከረው በሀገራችን የተከሰተው ሰፊ የአመፅና የግጭት ማዕበል ብሔራዊ ደህንነታችን የሚገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ በለውጥ ኀይሎችና በቀልባሾች መካከል የሚደረገው የሞት ሽረት ፍልሚያ የሚቋጭበት ሂደት ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከሁሉ አስቀድሞ በታቀደና በተደራጀ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ መሆናችን መቀበል ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው እርምጃ በየስፍራው የተለኮሰው እሳት እንዳይዛመት መከላከል ነው፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ብሔራዊ የዘመቻ እቅድ አውጥቶ ያለውን ሀብትና ጉልበት በማሰማራት ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ ከሰላማዊ አማራጮች በተጓዳኝ የግጭት ተዋናዮችን፣ የአመፅና የሽብር ቡድኖችን፣ የጦር አበጋዞችን አደብ የሚያስገዛ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ግልፅና ስውር የጥፋት መረቦችን መበጣጠስ፣ መዋቅሮችን ማፍረስ፣ ሀብቶችና መገልገያዎችን ማገድና መውረስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የግጭቱን ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ መዘዞች መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለግጭቱ ሰለባዎች አፋጣኝ ቁሳዊና ሥነልቡናዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡
መንግሥት ከእለት እለት ግጭቶችን በመከላከልና በማስወገድ፣ አስተማማኝና ሰላማዊ ሥርዓትን በመመሥረትና የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝብ አመኔታን ያጎለብታል፡፡ ለዚህም ባህላዊና ልማዳዊ እሴቶችንና ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን የመፍትሔው አካል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ ሁልጊዜም የሰላም ወገን በመሆኑ በክልልና በአካባቢ ደረጃ በሰላምና መረጋጋቱ ሂደት የሚሳተፍበትን መንገዶች መቀየስ፣ ጥፋተኞችን እርቃናቸውን ማስቀረትና ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

በመካከለኛ ወቅት ውዥንብርና የግጭት ስጋትን ማስወገድና በማህበረሰቦች መካከል መተማመንን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ከቁጥጥር ውጭ ያሉ የኀይል ማዕከላትንና የግጭት ምንጮችን የሚያመክኑ እርምጃዎች መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብም ደህንነት እንዲሰማው በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ለሕዝብ ጥቅምና ለሕግ ተገዥነት መሰለፋቸውን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች፣ በሲዳማና በወላይታ፣ በኦሮሚያና በጋሞ እንደታየው በጎ እርምጃ በይነ ክልላዊና ማኅበረሰባዊ መፍትሔዎችንም ትስስሮችንም ማጎልበት ያሻል፡፡
ቀጣዩ ደረጃ ዘለቄታዊ የግጭት ማስወገጃ አስተማማኝ የሰላም ግንባታ ነው፡፡ ለዚህም የችግሩን መሠረታዊ ምክንያቶች በጥንቃቄ መለየትና በየደረጃው በአግባቡ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በዋነኝነት ወያኔ ተከሉን የተዛባ የጎሳ ሥርዓትና መርዘኛ የጥቅመኝነት አስተሳሰብ ማስተካከል ነው፡፡ ዘውጋዊነት በአግባቡ ከተያዘ ገንቢ ማኅበራዊ ኀይል ቢሆንም፣ ቅጥ ያጣ ጎሰኝነት ግን የማኅበረሰብ ጠንቅ ነው፡፡ ስለዚህም በንዑሳዊ ማንነቶችና በብሔራዊ የጋራ ማንነት መካከል ኅብርና ሚዛን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱን መዋቅራዊም፣ ሕጋዊም፣ ተግባራዊም ጉድለቶች በማረም በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሐቅ የሚያገናዝብ ሥርዓት መመሥረት ይገባል፡፡ አስተማማኝና ሁሉን ዐቀፍ የእርቅ ማዕቀፍና ከማንነት ይልቅ በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ የድርድር ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ በክልሎች አወቃቀር፣ በፌዴራልና ክልላዊ መንግሥታት፣ እንዲሁም በቡድንና በግል መብቶች መካከል ሚዛን የሚያስጠብቅና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ነው፡፡