አዲስ አበባ ላይ ታሪካዊና ወደር የለሽ የተባሉ ሕንፃዎችን በእድሳት ስም በቀለም የማበላሸት ወንጀል ከመሐንዲሶችና ከአርኪቴክቸሮች ተቃውሞ ገጠመው

May be an image of 1 person
በኪዳኔ በየነ ህንፃ ላይ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል የዛሬ አራትና አምስት ዓመት በምኒልክ ሀውልት ላይ ከተፈፀመው ጋር ፍፁም ተመሣሣይ ነው። – ረዳት ፕ/ሮ በቀለ መኮንን (ሠዓሊ፣ ቀራፂና መምህር)
ሳያውቁ በስህተት፣ ወይስ አውቀው በድፍረት?
በአርክቴክት ዮሀንስ መኮንን
መቼም ይህንን የመሰለ ስህተት የሚፈጠረው አንድም ተገቢው ባለሙያ በተገቢው ቦታ ሳይቀመጥ ሲቀር ወይም “አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት የባሏን መጽሐፍ አጠበች” እንደሚባለው ዓይነት ድፍረት የሚወልደው አለማወቅ ነው።
የአዲስ አበባን መልክ ከወሰኑ የግንባታ ገጽታዎች (Built Environment) መካከል የኪነ ህንፃ ባለሙያዎች “የ1960ዎቹ” በማለት የሚጠሯቸው የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ህንፃዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እነኚህ ሕንፃዎች እስከዛሬም ድረስ ወደር ባልተገኘላቸው ከግንባታ ጥራት እና ከግንባታ ቁሳቁስ አመራረጣቸው በተጨማሪ ዘመናዊ የዲዛይን ጽንሰ ሀሳባቸው (Modern Style) ተለይተው ይታወቃሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪቴክቸር፣ የሕንፃ ግንባታ እና የከተማ ልማት ትምህርት ቤት (EiABC) መምህራን እና ተማሪዎች የእነኚህን ህንፃዎች የዲዛይን ሀሳብ፣ ንድፍ፣ የግንባታ ቁሳቁስ እና አሁን ስለሚገኙበት ሁኔታ በዝርዝር በማጥናት Addis Modern የሚል ማስተማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። ዛሬም ድረስ በርካታ የኪነሕንፃ ተማሪዎች የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ምርምር ሥራዎቻቸውን እያጠኑባቸው ይገኛሉ።
በአጭር ቃል የእነኚህን ታሪካዊ ህንፃዎች መልክ በዚህ መልኩ መቀየር ማሳመር ሳይሆን ማበላሸት ነው። ያገኙትን ሕንፃ ሁሉ ቀለም እየቀዱ መለቅለቅ ለስልጣኔ እና ለሳይንስ ባዕድ መሆንን ያሳያል። ይህ እንዲሆን የወሰኑት ሰዎች (ባለሙያ አይመስሉኝም) የግብረ ሕንፃዎቹን ታሪካዊ እና ኪነ ሕንፃዊ ፋይዳ ካለመረዳት “ከቅንነት ነው ያደረጉት” ብዬ በመገመት የባለሙያዎችን ሀሳብ በማድመጥ በፍጥነት እንደሚያርሙ እና ወደ ነባር መልካቸው እንደሚመልሷቸው ተስፋ አደርጋለሁ።
ካልሆነ ግን ጉዳዩ አውቆ የማጥፋት አባዜ በመሆኑ “ሳያውቁ በስህተት” ሳይሆን “እያወቁ በድፍረት” መሆኑን ለማመን እንገደዳለን።

“…ሙያዊ ነውር..” – ረዳት ፕ/ሮ በቀለ መኮንን (ሠዓሊ፣ ቀራፂና መምህር)

በዚች ሰዓት በኪዳኔ በየነ ህንፃ ላይ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል የዛሬ አራትና አምስት ዓመት በምኒልክ ሀውልት ላይ ከተፈፀመው ጋር ፍፁም ተመሣሣይ ነው። የምኒልክ ሀውልት ያኔ ሲጫወቱበት መልኩን እንዲያብረቀርቅ አድርገው ነበርና የላዩን ወርቅማ ቀለም እንጂ የውስጡን ወንጀል ብዙሃኑ እስከዛሬም ያወቀ አይመሥለኝም።

የነሀስ ሀውልት ያውም ያደባባይ ቅርፅ በየትኛውም ዘመን በየትኛውም ሀገር ቀለም ተቀብቶ አያውቅም። ሙያዊ ነውር ስለሆነ። ነገር ግን ኬሚካላዊ ሂደትን አልፎ የራሱ ቀለም እንዲኖረው የሚደረግበት ነባር ስርዓት አለው ።

እየነገርናቸው አሻፈረኝ ብለው ነሀስን ቀለም የቀባች ብቸኛ የደንቆሮ አገር ሰዎች አርገው ያዋረዱን እነሆ አሁን ደግሞ ይሁነኝ ብለው ከነመልኩ አልቆለት የተገነባን ህንፃ ዳግም የጥፋት ቀለም እየለቀለቁት ነው ፣ እግዚኦ !

አሁን እንኳ እንደያኔው ብዙ የማስጠንቀቂያ ጩኸት አልተሰማም።ለነገሩ እነሱ የቀደመ ጩኸትም ሆነ የዘገየን ምክር ከጉዳይ ባይጥፉም።

የምኒልክ ሀውልት ከተተከለ ጀምሮ ጣሊያኖች በጠላትነት አንዴ ሲያበላሹት እኛ ግን ተዉ እየተባልን በድንቁርና ሶስት ጊዜ አበላሽተነዋል። የመጨረሻው ብልሽት የዛሬ አራት ዓመት ከመፈፀሙ በፊት እባካችሁ ሀገሪቱን አታዋርዱ ስራው መካሄድ ያለበት በዚህ በዚህ መንገድ ብቻ ነው የሚል ብዙ ኡኡታ ከጊዜው ባህል ሚኒስትር እስከ ሳይት ላይ ሰራተኛ እንዲደርሰው ተደርጎ ነበር። ማንም ከቁብ ሳይቆጠር ለሳንቲም ቅርምት ሲባል አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥፋት ተፈፅሞበት ለጥፋት መሸፈኛ እንደ ስኒ የሚያብረቀርቅ ወርቅማ ቀለም ይለቀለቅ ዘንድ ተፈርዶበት ይኸው አሁን በሙቀትና በቅዝቃዜ እየረገፈ ገመናው መታየት ጀምሯል።ዝገቱም በቅርብ ወራት መገለጥ ይጀምራል።አሻግሮ ማለም ደክሞን የዕለት የዕለቱን ብቻ እያየን ላብረቀረቀ ሁሉ ያለጥርጥር እንደምናጨበጭብ ሹመኛና ጉልበተኛ አወቀብን። አራዳ ጊዮርጊስ ሙያዊ ወንጀል መፈፀሙን ብዙዎቻችን እስከዛሬም የምናውቅ አልመሠለኝም።

ቤትን ወይም ሀውልትን ሰርቶ ከማቆም ቀጥሎ የሚመጣው ዝርዝር የፍፅምና ጉዳይ ለሀገራችን ጉልበተኞችና በላተኞች የቅንጦት እንጂ የህይወት ዋነኛ ክፍል መሆኑ እስቲገለጥላቸው ክርስቶስ ተመልሶ እንዳይመጣ እሰጋለሁ።