ለላሊበላ ቅርሶች እድሳት ብቻ 300 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል የመንግስት በጀት 37 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው

የላሊበላ ቅርሶች ጉዳይ —

• ለላሊበላ ቅርሶች እድሳት ብቻ 300 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፤
• መንግስት በአገር አቀፍ ላሉ ቅርሶች የያዛው በጀት ግን 37 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የባህል ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ጌቱ አሰፋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በቅርሶች ላይ አደጋ ሲጋረጥ ዩኔስኮ የተለያዩ አገራትንና ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማትን ያስተባብራል። በአገሪቱ ላይ ለተመዘገቡ ቅርሶች በሙሉ ግን በዋናነት የሚመለከተው የአገሪቱን መንግሥት ነው፡፡

የላሊበላ ቅርሶች ላይ ያጋጠሙትንም ችግሮች ለመፍታት አሁንም ፍቃደኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌቱ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንም ቢሆን በዓለም ላይ የታወቁ አማካሪዎችን ቀጥሮ ሥራዎችን ጀምሯል፤ ቀጣዩ ውሳኔም የመንግሥት በመሆኑ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቅርሶቹ ላይ የተሠራው ጣሪያ ፀሐይና ዝናብ ለመከላከል በጊዜያዊነት ነው፤ ማንም ቢሆን ጣሪያው እንዲቆይ የሚፈልግ የለም›› ያሉት አቶ ጌቱ፤ ብዙ ጊዜ ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት በሚደረግበት ጊዜ በጣሪያው መነሳት ያምናሉ፡፡ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ግን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ የሚታወቅ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ እንደገለጹት፤ ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ ሦስት ዓመት በሚፈጀው የጥገና ሂደት የሚያስፈልገው 300 ሚሊዮን ብር ቀዳሚው ፈተና ነው ብለዋል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ለቅርሶች የተያዘው በጀት 37 ሚሊዮን ብር ነው። ይህንን በጀት ለላሊበላ ቅርሶች ጣሪያ ብቻ ከሚያስፈልገው 20 ሚሊዮን ብር አንጻር አነስድተኛ ስለሆነ የተጠቀሰውን በጀት ለማሟላት የሁሉም የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል፡፡

የቅርሶቹን ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢነት በመገንዘብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ባካሄዱት ሰልፍ በአስቸኳይ ፋይናንስ የማፈላለግና ፕሮጀክቶቹን የማስቀጠል ሥራ እንዲሠራ ማሳሰባቸውን ጠቅሷል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ ክልሉ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ቅርሶቹን ሙሉ በሙሉ ጠግኖ በማጠናቀቅ ጊዜያዊ መጠለያዎችን የማንሳቱን ሥራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ድንቅ የኪነ ህንፃ አሻራ ያረፈባቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲናት በ1979 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

*******************************
(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE