ቁም ነገሩ የብሮድካስት ባለስልጣኑ እንደ ቀድሞ ማስፈራራት እንደማይችል ማወቁ ላይ ነው (ስዩም ተሾመ)

ከብሮድካስት ባለስልጣን ለLTV እና ቤቲ ታፈሰ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያና የቪዲዮ ምስሉን ከኢንተርኔት ላይ እንዲያወርዱ መደረጋቸውን የሰማሁት ከሌላ ሳይሆን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው የጣቢያው ሰራተኛ ነው። ይህ ሰራተኛ ዛሬ ልክ ከቀኑ 8፡41 ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደከሰሳቸውና የጣቢያውን ኃላፊ ወደ ቢሮ ጠርቶ ቃለ-ምልልሱ “ለአንድ ወገን ያደላ ነው! የቪዲዮ ምስሉ በአስቸኳይ ይውረድ” ብሎ እንዳዘዘው ነገረኝ።

እኔም “በቀጥታ እንዲመጡ ንገሯቸው! ለጣቢያው ጉዳዩን አስመልክቶ በደብዳቤ ያሳውቋችሁና እናንተም በደብዳቤ ምላሽ ስጡ” የሚል ምክር ሰጠኋቸው። ይህን ያልኩበት ምክንያት እንዲህ ያለ በእብሪት የተሞላ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ በጓሮ በር ያስተላለፈው የብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ኃላፊ ጉዳዩ አደባባይ ሲወጣ አንዳች ነገር ትንፍሽ እንደማይል እርግጠኛ ስለነበርኩ ነው።

አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ኃላፊ በጣቢያው ሥራ ላይ በቀጥታ ጣልቃ-ገብቶ እንዲህ አድርጉ፣ ያንን ቪዲዮ አውጡ ሌላኛውን አውርዱ የማለት ስልጣን የለውም። በመስሪያ ቤቱ መደበኛ አሰራር እንዲህ ያለ ትዕዛዝ ሆነ ማስጠንቀቂያ አይሰጥም። ስለዚህ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የጣቢያውን ሰራተኛ ቢሮ ጠርቶ በወረቀት ላይ ማስፈር የማይችለውን ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ በቃሉ ተናገረ። በዚህ የተደናገጡት የጣቢያው ኃላፊዎች የቃለ-ምልልሱን ቪዲዮ ከኢንተርኔት ላይ አወረዱት።

ነገሩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥቶ የብዙዎች መነጋገሪያ ሲሆን ግዜ ቀድሞ በማንአለብኝነት ሲያስጠነቅቅና ሲያስፈራራ የነበረው ሰውዬ ወደ ጣቢያው ደውሎ “የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እስካልደረሳችሁ ድረስ የብሮድካስት ባለስልጣን ማስጠንቀቂያ ሰጠን ብላችሁ መናገር አትችሉም” ብሎ ሊለማመጥና ሊያስፈራራ እንደሚችል የታወቀ ነው።

የጣቢያው ኃላፊዎች ይህን በፍርሃት ተቀብለው “ማስጠንቀቂያ አልተሰጠንም” ብለው ለቢቢሲ ቢናገሩም የቃለ-ምልልሱን ቪዲዮ ከኢንተርኔት ላይ ማውረዳቸውን ግን አልካዱም። ቪዲዮውን ያወረዱት ቤቴልሄም ላይ እየደረሰ ባለው ዛቻና ማስፈራሪያ ምክንያት ቢሆን ይህን ማድረግ የነበረባቸው ዛሬ ሳይሆን ከአመስት ቀናት በፊት ነበረ። ለማንኛውም የትኛውም የመንግስት ባለስልጣን እንደ ቀድሞ እያቅራራና እያስፈራራ መኖር የማይችልበት ቀን ላይ መድረሳችንን በተግባር ተመልክተናል። ይኼው ነው!!!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE