በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ በልማት ሥም ታሪካዊ ሥፍራዎችን ማውደም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየ ክፍለ ከተማው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቅርስ ማውደም እስከመቼ!? –  ፍትሕ መፅሔት

መንግሥት በኩል እየተከናወነ ያለው ብሔራዊ አገራዊ ቅርሶችን በቸልተኝት የማደብዘዝና የማዳፈን፤ ሆን ብሎና አቅዶ የማክሰምና የማፈራረስ መርሃ-ግብሩ መቋጫ ያጣ ሆኗል። በተለይ በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ በልማት ሥም ታሪካዊ ሥፍራዎችን ማውደም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየ ክፍለ ከተማው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሕዝብ በልማት ሥም ቅርስ እንዳይፈርስ እየወተወተ፣ ብዙሃን መገናኛዎች እየዘገቡ፣ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት (እንደ ምሳሌ አዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ) ለአስፈፃሚው መንግሥታዊ አካል ተቃውሞን እያሰማ፣ ፍርድ ቤት እግድ አውጥቶ “ማፍረሱ ይቁም” የሚል ትዕዛዝ እየሰጠ ሳይቀር፤ በርካታ ቅርሶች እንዲፈርሱ ተደርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያን የሚያህል ታሪካዊ አገር ትላንት የተፈጠረች ለማስመሰል የሚደረገው ፖለቲካዊ አሻጥር፣ በአስፈፃሚው አካል ውስጥ በተሰገሰጉ ጸረ-ኢትዮጵያ አመለካከት ባላቸው ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች እየተተገበረ ስለመሆኑ መረጃዎች አሉ።

ሰሞኑን ደግሞ በአገሪቱ ቀደምት የሆነውንና በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገበውን የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) አሁን ከሚገኝበት ዋና ቦታ ለማፈናቀል ቀጭን ትዕዛዝ ወርዷል። ኮሜርስ የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ዐርበኞችና በቃል ኪዳን አገራት ትብብር ተቀጥቅጦ ከተባረረ በኋላ፣ በ1935 ዓ.ም በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ባለሙያዎትን ለማስመረቅ ሲባል፣ በአገሪቱ ታሪክ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ የተቋቋመ የመጀመሪያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ትምህርት ቤት በዘርፈ ብዙ የቢዝነስ ትምህርቶች ከሠርተፍኬት የጀመረ ሲሆን፤ በጊዜ ሒደት በየዘመናቱ በሚያደርገው የፍላጐት ዳሰሳ ጥናቶች የዲኘሎማ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ የድህረ-ምረቃ የትምህርት ክፍል መሥርቶ በሁለተኛ ዲግሪ (የማስተርስ)፤ እንዲሁም የዶክትሬት (የፒ.ኤች.ዲ) ኘሮግራሞች በመክፈት ከእነ ጥንካሬውና መልካም ስሙ፣ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ለ78 ዐመታት በስኬት የተጓዘ ቀዳሚው ተቋም ነው።

ዘግይተው ለተቋቋሙ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆችም ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ልምዱንና ‹‹ካሪኩለሞቹን›› በማጋራት ለአገርና ለሕዝብ ከፍተኛ ባለውለታ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ በተቃራኒው፣ መንግሥት ታሪክና ቅርስ የማወደም ሃራራውን በኮሜርስ ላይ ሊወጣ ከጫፍ ደርሷል። የተቋሙ ህንፃዎች ለምን መፍረስ እንደሌለባቸው ከሚመለከታቸው አካላት የቀረቡ ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

የንግድ ስራ ት/ቤት በጠቅላላ ስሙም ሆነ ነባር ሕንጻዎቹ በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገቡ በመሆናቸው፤

ትምህርት ቤቱ ዐዲስ ዘመናዊ ሕንጻ ለመማሪያ ብሎ የገነባና ያዘጋጀ ሲሆን፣ ይህ ዐዲስ ህንፃ ለሌላ ዓላማ/ ጉዳይ ለማዋል ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፤

ከ1ዐዐ በላይ መምህራን፣ ከ2ዐዐ በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች፤ እንዲሁም ከ5ዐዐዐ /አምስት ሺሕ/ በላይ ተማሪዎች ለማዘዋወር ሰፊ ቦታና ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቅ በመሆኑ፤

ት/ቤቱ ለፋይናንስ ተቋማት ልማት ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙና ለረዥም ዐመታት የቆየ አገልግሎትና የዓላማ ተመጋጋቢነት የተነሳ ቦታው ስትራቴጂካዊ የሥራ ግንኙነትና ጥምረት ያለው በመሆኑ፤ ለበርካታ ዐመታት የተገነባ የሥራ ግንኙነት ሳይቋረጥ መቀጠል ስላለበትና በዚህ ግንኙነት የሚገኝበት ቦታ የሚሰጠው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ፣ ተቋሙ አሁን በሚገኝበት ግቢ ስሙንና ቅርስነቱን ጠብቆ ለአገር፣ ለሕዝብና ለትውልድ የሚሰጠውን አገልግሎት ቢቀጥል አገርና ሕዝብ አትራፊ ስለሚሆኑ ነው።

በሌላም አንፃር፣ የንግድ ሥራ ት/ቤትን የሥራ እና የትምህርት ማዕከል አድርገው ሕይወታቸውን የሚመሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። በንግድ ሥራ ት/ቤት በቂ ልምድ ያላቸው 100 የሙሉ ጊዜ ቅጥር መምህራን ሲኖሩ፣ ከዚህ ውስጥ 14 ሴቶች እና 86 ወንዶች ናቸው። በትምህርት እርከን 4 ተባባሪ ኘሮፌሰሮች፣ 32 ረዳት ኘሮፌሰሮች፣ 6ዐ ሌክቸረሮች፣ 3 ረዳት ምሩቃንና 1 ቴክኒካል አሲስታንት ይገኛሉ።

የአስተደደር ሠራተኞች በቁጥር 151 ሲሆኑ፤ በትምህርት ዝግጅት 4 በማስተርስ፣ 31 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 57 ዲኘሎማና 59 በት/ቤቱ የሚገኙ የአካዳሚክም ሆነ የአስተዳደር ሠራተኞች በጠንካራ የሥራ ባህል የሚታወቁ ናቸው። ከት/ቤቱ ባህሎች አንዱ ጠንካራ የሥራ ባህል ማዳበሩ እንደሆነም ልብ ይሏል።

በትምህርት ተቋሙ ውስጥ ያለውን የተማሪ ብዛት ስንቃኝ፣ የ2ዐ12 ዓ.ም ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት (ሴሚስተር) በቅድመ ምረቃ ኘሮግራም በመደበኛ ለ771፣ በማታ ለ1,579፣ የማስተማር አገልግሎት የሰጠ፣ በማስተርስ ኘሮግራም በመደበኛ 183፣ በማታ ለ1,ዐ58፣ በርቀት ለ783/፣ በፒኤችዲ ለ38 በጠቅላላ 4,45ዐ / አራት ሺሕ አራት መቶ ሃምሣ/ ተማሪዎችን የትምህርትና የማማከር አገልግሎቶችን ሰጥቷል።

የንግድ ሥራ ት/ቤት ስድስት ህንጻዎች ያሉት ሲሆን፣ በውስጣቸው የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የኮምፒውተር ላብራቶሪዎች፣ ቢሮዎች፣ ካፊቴሪያዎችና መጸዳጃ ቤቶች ይገኙባቸዋል። ት/ቤቱና አብዛኛዎቹ ህንፃዎች በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው። በተጨማሪም፣ ዐዲሱ ህንፃ ለመማር ማስተማር ጉዳይ ብቻ የተሠራ በመሆኑ፣ ለሌላ የፋይናስንስ አገልግሎት ለምሳሌ እንደ ባንክ ላሉ መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ወጪና እድሳት ካልተደረገለት በቀር ሊውል የሚችል አይደለም። ግቢውም መፍረስ እንዳይችል በቅርስነት የተመዘገበ ስለሆነ፤ በላዩ ላይ ሌላ ህንፃ ለመገንባት ሕጉ አይፈቅድም።

ት/ቤቱ የማማከር፣ የስልጠና፣ የሥራ ቅጥርና ዕድገት ፈተናዎችና ነፃ የማኀበረሰብ አገልግሎቶች የሚያስተባብርበት የተደራጀ ቢሮ ያለው ሲሆን፤ ክህሎትና እውቀት ባዳበረባቸው የቢዝነስ ዘርፎች ለበርካታ ድርጅቶች፣ በተለይ ደግሞ ለባንኮች እና ኢንሹራንሶች በጣም ብዙ አገልግሎቶች የሚሰጥ ተቋም ነው።

ከዚህም የተነሳ የዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ከማጠናከርም በላይ፤ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያገኘውን ገቢ ከዐቅም ውስንነት በመንግሥት በጀት ሊሸፈኑ ያልቻሉ የተቋሙ ወጪዎችን ከመሸፈን አልፎ፤ ከፍተኛ ታክስ የሚያስገባ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በየጊዜው ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ የሚደጉም ነው። በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ / ማዕከል/ በ2010 ዓ.ም 8 ሚሊዮን ብር፣ በ2ዐ11 ዓ.ም 15 ሚሊዮን ብር፣ እንደዚሁም በ2ዐ12 ዓ.ም 5.2 ሚሊዮን ብር ገቢ አድርጓል።

በጥቅሉ “ፍትሕ መጽሔት” ኮሜርስ በአገሪቱ ካሉ ታሪካዊ ተቋም ግዘፍ-የሚነሳ ከመሆኑ በዘለለ፤ እጅግ ውድ የሕዝብ እና የአገር ቅርስ በመሆኑ፣ መንግሥት ለማፍረስ የተነሳበትን ሰይጣናዊ አመለካከቱን አባርሮ፣ ወደ ልቦናው እንዲመለስ ለማሳሰብ ትወዳለች። ቅርስ ማወድም፣ ከጁንታው አገር የማፍረስ ተግባር ተለይቶ አይታየም።

ከኮሜርስ ላይ እጃችሁን አንሱ!