በወልቃይት ፣ በዋግ ፣ በራያ ግንባር ከባድ ውጊያ ስለመኖሩ ተሰምቷል

በወልቃይት ግንባር ፣ በዋግ ግንባር፣ በራያ ግንባር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል። በተለይም በምስራቁ ቀጠና ላይ ከባድ ውጊያ ስለመኖሩ ተሰምቷል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ውጊያ ባለበት ግንባር ሁሉ ህወሓት ሽንፈትን እየተከናነበ እንደሚገኝ እየገለፀ ይገኛል። ነገር ግን ከውጊያ ስትራቴጂ አንፃር ቦታዎችን መያዝ እና መልቀቅ ሊኖር እንደሚችል በማንሳት እስካሁን ህወሓት አሸንፎ የያዘው ቦታ እንደሌለ ገልጿል።

በቆቦ እና ዙሪያዋ ውጊያ መኖሩን ያሳወቀው የአማራ ክልል መንግስት ህወሓት ላይ ድል እየተጎናፀፍን ነው ብሏል። የህወሓት ኃይል ይዧቸዋለሁ ባላቸው ቦታዎች ውጊያ መቀጠሉን የህወሓትም የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች መኖራቸውን አሳውቋል።

ውጊያ እየተደረገ ያለው እጅግ ከከፍተኛ የሰው ቁጥር ነው ፤ በብዛት ሆነው ነው እየመጡ ያሉት ብሏል የክልሉ መንግስት።

እየተደረገ ባለው ጦርነት ከፍተኛ የሰው ቁጥር እያለቀ ነው የሚለው የአማራ ክልል ህወሓት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ እድሜያቸው ያልደረሰ ልጆችን በግዳጅ እያዘመተ ይገኛል ብሏል።

የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን መላክ የለባቸውም የተላኩትም የት እንደደረሱ መጠየቅ አለባቸው ሲል ገልጿል። የአማራ ክልል ህዝብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝቡ ለህልውና ዘመቻው እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን አንስቷል።

በሌላ በኩል ከፌዴራልና ክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ጦርነት ላይ ነኝ የሚለው የህወሓት ኃይል በተለያዩ ግንባሮች ወደፊት እየተጠጋ መሆኑን እየገለፀ ሲሆን የተለያዩ ቦታዎችንም እየተቆጣጠርኩ ነው ብሏል ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እድሜያቸው ያልደረሱ ልጆች በጦርነቱ ውስጥ እየማገደ ነው ለህልውናችን ስልን ጦርነቱን እንቀጥላል ብሏል።