ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋነኛ አውራ ጎዳና እና የባቡር መስመር በአካባቢው ወጣቶች ተቃውሞ ተዘጋ

ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው ዋነኛ አውራ ጎዳና እንዲሁም ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ ቁሳቁሶች የሚጓጓዙበት የባቡር መስመር መዘጋቱን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገለጹ።

አውራ ጎዳናው ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ የተለያዩ ሸቀጦች ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ነው። ሮይተርስ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ መንገዱና የባቡር መስመሩ የተዘጋው ቅዳሜ ዕለት በሶማሌ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በሚቃወሙ የአካባቢው ወጣቶች ነው።የተሽከርካሪዎች መንገዱ እና የባቡሩ መስመሩ መዘጋት ላይ እስካሁን የፌደራሉ መንግሥት ያለው ነገር የለም።

የሶማሌ ክልል መስተዳደር ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ እንደተባለው፤ የአጎራባች ክልል አፋር ሚሊሻ ጥቃት ፈጽመዋል። የንብረት ውድመትም አድርሰዋል። ባለፈው ቅዳሜ በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በሆነ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ቦታ በተፈፀመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሮብሌ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤ ቅዳሜ ሐምሌ 17/2013 ዓ. ም በአፋር ክልል ሥር በሚገኘው እና በርካታ የሶማሌ ብሔር ተወላጆች ይኖሩበታል ባሉት ከተማ በንጹሃን ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የባቡር መስመሩ እና የመንገድ መዘጋቱን የሚያመላክቱ በርካታ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅብራዊ ሚዲያዎች ላይ ተሰራጭተዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ፎቶዎች ተቃዋሚዎች የባቡር መስመሩን እና ዋና አውራ ጎዳናውን በድንጋይ በተቃጠሉ ጎማዎች እና በአፈር ዘግተው ያሳያሉ። የባቡር መስመሩ እና መንገዱ የተዘጉትም የሶማሌ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ግድያን በተቃወሙ የክልሉ ተወላጆች መሆኑ ተመልክቷል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ የመንገድ እና የባቡር መስመር መዘጋትን በተመለከተ “ከወጣቶቹና ከሕዝቡ ጋር እየተወያየን ነው። መንገዱና የባቡር መስመሩ ዛሬ እንዲከፈት እየሠራን ነው” ሲሉ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ እንደሰጡ ሮይተርስ ዘግቧል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ፤ ጥቃት ተፈጸመበት ያሉት ገብረኢሴን ከተማን ጨምሮ ፎና እና አደይቱ የሚባሉ ከተሞች በሁለቱ ክልል የይገባኛል ጥያቄ እንደሚነሳባቸው ገልጸዋል። ቅዳሜ የደረሰው ጥቃት መንስኤም በሁለቱ ክልሎች መካከል በቆየው የግዛት ይገባኛል ጉዳይ ነው ብለዋል። በሶማሌ እና በአፋር ክልል መካከል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ ግጭቶች መነሳታቸው አይዘነጋም። ቅዳሜ እለት ደረሰ ስለተባለው ጥቃት ከአፋር ክልል በኩል መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ወደተለያዩ የክልሉ ባለሥልጣናት ስልክ በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም።

ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚያገናኘው አውራ ጎዳና እና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መንገድ መዘጋታቸውን የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ። የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር አመራር አባል ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲን የሚያገናኘው መንገድ በመዘጋቱ ከ1,500 በላይ ተሽከርካሪዎች በድሬዳዋ ከተማ መቆማቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።ከሽንሌ እስከ ደወሌ ያለው እና ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚያገናኘው አውራ ጎዳና መዘጋቱን አቶ ዳመነ ተሾመ የተባሉ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ከኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ዳመነ መንገዱ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በመዘጋቱ ከ1500 በላይ አሽከርካሪዎች በድሬዳዋ ከተማ ለመቆም መገደዳቸውን ለዶይቼ ቬለ የአዲስ አበባ ወኪል ሰለሞን ሙጬ ተናግረዋል።

የሶማሌ እና የአፋር ክልሎችን አቋርጦ የሚያልፈው አውራ ጎዳና ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ሸቀጥ 95 በመቶ ገደማውን የምታስገባበት እና የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት የደም ሥር የሚባል ነው። አቶ ሙስጠፋ የተዘጉትን መንገዶች ለማስከፈት ለተቃውሞ ከወጡ ወጣቶች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ለሬውተርስ ተናግረዋል። የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በሲቲ ዞን ገርበኢሴ የተባለች አነስተኛ ከተማ ቅዳሜ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት ለጥቃቱ ኡጉጉሙ የተባለ ታጣቂ ቡድን እና የአፋር ልዩ ኃይልን ተጠያቂ አድርጓል።የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች ገዳማይቱ፣ እንዱፎ እና አዳይቱ የተባሉት ቀበሌዎች ባለቤትነት ለአመታት የዘለቀ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል። ሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ድንገተኛ ግድያዎች በተደጋጋሚ ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል።