ሥራ አጥነትና ብሔራዊ አለመረጋጋት

ሥራ አጥነትና ብሔራዊ አለመረጋጋት ፥ ሳምሶን ኀይሌ

“… የሥራ አጥነቱን ችግር የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሊፈቱት አይችሉም፡፡ አቅሙም ጉልበቱም የለም፡፡ እየተበራከተ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ሊቀረፍ የሚችለው የግድ የውጭ ባለሁብቶች እንዲገቡ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ፣ በሩ ይከፈት የምለው ለእኔ ሳይሆን፣ ለቄሮና ለፋኖ ነው፡፡”

ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት ለሪፖርተር ጋዜጣ (ጳጉሜን 4/2010) የሰጡት አንጋፋው ባለፀጋና የግሉ ዘርፍ ተዋናይ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ብዙአየሁ ሁሉ ብዙዎችን የአገራችንን ባለንብረቶች የሚያሳስባቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ አለመያዝ ወይም የሥራ አጡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ነው፡፡

የአገራችን የሕዝብ ቁጥር ያለማቋረጥ እየጨመረ ነው፤ የትምህርት ጥራቱ ሁኔታ እዚህ ግባ የማይባልም ቢሆን በጣም በርካታ ወጣት የኹለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ትምህርት እየጨረሰ ይመረቃል፡፡ ይህን በየጊዜው ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚመረቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጣት የሚሸከም (‹አብዞርብ› የሚያደርግ) ኢኮኖሚ ግን የለንም፡፡ ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡

ተምሮ ሥራ አጥ የሚሆን ወጣት ለተስፋ መቁረጥ የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ ስሜታዊ ለሆኑ አክራሪ የፖለቲካ አጀንዳዎች በቀላሉ የመማረክ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ በተለይ አካራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች ሥራ አጥ ወጣቶችን ዋና የአመጽ ማቀጣጠያዎች በማድረግ በቀላሉ ይጋልቧቸዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያና በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች፣ ሥራ አጥ ወጣቶች የጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኞች መሣሪያ ሆነው ምን ያህል ፋብሪካዎችን እንዳጋዩ፣ ስንት ተሸከርካሪዎች በእሳት እንደተለኮሱና ከጥቅም ውጪ እንደሆኑ፣ ምን ያህል ዝርፊያና ቅሚያ እንደተካሄድ፣ በዚህም ምን ያህል ኢንቨስተሮች ሥራቸውን አቋርጠው እንደወጡ የሚታወቅ ነው፡፡ መንግሥት በአመጽ ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንቨስትመንቶች መልሶ ለማቋቋም እጅግ ከፍተኛ ውጪ ማውጣቱን የፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሪፖርት መግለጹም አይዘነጋም፡፡

የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በአመጽና አለመረጋጋት ምክንያት እየቀነሰ መምጣቱ ተመልሶ ለሥራ አጥ ወጣቶቻችን መርዶ ሲሆን፣ አገሪቱም መልሳ ወደሌላ አመጽና አለመደጋጋት እንድትገባ ምክንያት ይሆናል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊረባረብ የሚገባው በዚህ ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ ላይ ነው፡፡ የትኛውም ዓይነት ዋጋ ተከፍሎ በአገራችን ሰፍኖ የሚገኘው ከልክ ያለፈ ሥራ አጥነት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ጊዜና ጉልበታቸውን የጽንፈኞች መሣሪያ በመሆን ማሳለፍ የለባቸውም፤ ወደ ሥራ የሚገቡበት መንገድ ሊመቻች ይገባል፡፡

ዛሬ፣ ኢትዮጵያዊያን በሚዘገንን መልኩ እርስ በርሳችን እየተጨካከንን ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ውብ ባህላችን በጣም ባፈነገጠ መልኩ ዜጎች በአደባባይ ተዘቅዝቀው እየተሰቀሉና በእሳት እየተቃጠሉ ነው፤ ነብሰ-ጡር ሴቶች እየተደፈሩ ነው፤ ሕፃናት በጭካኔ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያዊያን እንግዳ የሆነ የጭካኔ ተግባር የሚፈፀመው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ምክንያት አለው፡፡ አንዱ ምክንያት ሥራ አጥነት የወለደው በአገርና በራስ ላይ ተስፋ የማጣት ስሜት ነው፡፡ ዋናው ምክንያት ግን ይህ አይደለም፡፡ ዋናው ምክንያት እኔ ሥራ ያጣሁት እኔ ልሠራው እችል የነበረውን የሥራ ዕድል “ሌሎች” ስለወሰዱት ነው፤ መሬቴና ሀብቴ ስለተወሰደ ነው ወዘተ. የሚለው የጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኞች አስተምህሮ የፈጠረው የተንጋደደ ግንዛቤ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብታቸው አደጋ ላይ የወደቀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሚያንገበግብ ሁኔታ፣ አገራችን [በአገር ውስጥ] በሕዝብ መፈናቀል በዓለም ቀዳሚ የሆነችውም በዚህ አስተሳሰብ ምክንያት ነው፡፡

የአገራችን ሰላምና መረጋጋት ትልቁ ጠንቅ ከሥራ አጥነት የሚመነጭ ነው፡፡ ሥራ አጥነት ካለ ለአመጽ የሚመለመለና አውድም ሲሉት የሚያወድም፣ ግደል ሲሉት የሚገድል ኀይል ተገኘ ማለት ነው፡፡ ትልቁ አደጋ ይህ ነው፡፡ በዚህ ትልቅ ብሔራዊ አጀንዳ ላይ መረባረብ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የሥራ አጥነት አደጋ መፍትሔ ሳያገኝ ምርጫ አደርጋለሁ ማለት አገርና ሕዝብን ወደ አመጽ ቀጠና መውሰድ ነው፡፡ ቅድሚያ ለሚገባው አጀንዳ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሥራ አጥነት ብሔራዊ አደጋ ነው፤ ስለሆነም ከየትኛውም አጀንዳ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡