በዚህ ምርጫ ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች የተስተዋሉት የመንግስት ባህሪያት አይደገሙም – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) መሪ ጋር በተቀራራቢ ሰዓት ድምፃቸውን የሰጡት አምባሳደር ዲና በዚህ ምርጫ ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች የተስተዋሉት የመንግስት ባህሪያት አይደገሙም፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩው ለአሐዱ በሰጡት ማብራሪያ መሪዎች በምርጫ ተሸንፈው እንኳን ስልጣን አንለቅም የሚሉበትን አካሄድ የሚዘጋ የመጨረሻው ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡ እርሳቸው የሚወዳደሩት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የምርጫ ክልል ሀያ ቢሆንም ድምፃቸውን ግን የሰጡት በምርጫ ክልል 23 ላይ ነው፡፡

አምባሳደሩ የፓርቲያቸውን ፕሬዝዳንት ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት ምርጫውን ካሸነፉ እሰየው ካልሆነ ግን ያለማንገራገር ውጤቱን ለመቀበልና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ መሆናቸውን ለአሐዱ አረጋግጠዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በአመራርነት የተረከቡት ሰዎችና ሌሎች መስፈርቶች ይህ ምርጫን ለየት እንደሚያደርገው የተናገሩት አምባሳደሩ ከልምምድም አኳያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው ሲሉ አድንቀውታል፡፡አምባሳደሩ ፖለቲካ ፓርቲን ወክለው በምርጫ ሲወዳደሩ የመጀመሪያቸው መሆኑንም አሐዱ ለማወቅ ችሏል፡፡

አሐዱ ራድዮ 94.3