የአዲስ አበባ ህዝብ የሚወስነውን ውሳኔ እቀበላለሁ ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ የሚወስነውን ውሳኔ እቀበላለሁ ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ይህንን ለአሐዱ ያረጋገጡት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የምርጫ ክልል 20 ፓርቲያቸውን በመወከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩትና ወረዳ 6 አልማዝዬ ሜዳ የምርጫ ጣቢያ 02 ድምፃቸውን የሰጡት የቢሮው ሀላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ ናቸው፡፡
አቶ ገለታው እንደሚሉት ፓርቲያቸው የቅድመ – ምርጫው ሂደቱ አነስተኛ የተባለውን መስፈርት እንኳን ያላሟላ ነው፡፡ አሐዱ የቅድመ – ምርጫው ሂደት በዚህ መልኩ ከገመገማችሁት ለምን በምርጫው ትወዳደራላችሁ የሚል ጥያቄ አንስቶላቸዋል፡፡
የፓርቲው የቢሮ ሀላፊ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ ራስን ከምርጫ ማግለል መፍትሔ እንዳልሆነ ጠቅሰው አንድ ምርጫ የሚለካው ደግሞ በቅድመ – ምርጫው ሂደት ብቻ ሳይሆን በምርጫው ቀንና በድህረ ምርጫው ነው ብለዋል፡፡
ትናንት ሰኞ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የአዲስ አበባ ህዝብ የሚወስነውን ውሳኔ ፓርቲያቸው እንደሚቀበል ለአሐዱ አረጋግጠዋል፡፡ ፓርቲያቸው በአዲስ አበባ ባሉ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎችን እንዳሰማራም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡