በፓርቲ እጩ ወኪሎች ላይ ህገወጥ ተግባር የመፈፀም ሁኔታ መታየቱን ምርጫ ቦርድ አሳውቋል

‘አስተዳዳሪዎች ዛሬ የስራ ቀን አይደለም ወደቤት ግቡ’ – ወ/ሪት ብርቱካን 

ከምርጫ ጣቢያዎች ውጪ በተለይም በፖለቲካ ፓርቲ እጩ ወኪሎች ላይ በስፋት የሚደረጉ ህገወጥ ተግባራት በውጤቱ ላይ ትልቅ ተፅእኖ አላቸው።

ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት በሚመረምርበት ሁኔታ እና በሚያፀቅድበት ጊዜም ይህንን ታሳቢ አድርጎ ነው። ይሄን የመንግስት አካላት ማወቅ አለባቸው።

የመንግሥት አካላት ሰራተኞቻቸውን ፣ አስተዳዳሪዎቻቸውን ወደቤቶቻቸው እንዲገቡ ማድረግ አለባቸው።

ዛሬ የስራ ቀን አይደለም ከህግ አስፈፃሚዎች ውጪ፣ ከምርጫ ቦርድ ውጪ ፣ ከመሰረታዊ አገልግሎት ሰጪዎች ውጪ ደጅ ላይ የሚሰራ ማንኛውም አካል የለም።

ለሎጅስቲክስ እገዛ በሚያስገልግበት ጊዜ መገኘት አለባቸው ነገር ግን ምርጫ ጣቢያ አካባቢ ተገኝተው ፣ ወይም የምርጫ ክልል ፅ/ቤት ተገኝተው /ሌላ ቦታ ተገኝተው የእጩዎችን ወይም የወኪሎቻቸውን ተግባር የሚያሰናክሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ ተቀባይነትም የለውም፤ ህገወጥ ነው።

በአማራ እና በደቡብ ክልል በጣም አሳሳቢ በሚባል ደረጃ፣ በአፋር ክልል ደግሞ በመለስተኛ ደረጃ በፓርቲ እጩ ወኪሎች ላይ ህገወጥ ተግባር የመፈፀም ሁኔታ መታየቱን ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በየምርጫ ጣቢያው ታዛቢ ወኪሎቻቸውን አስቀምጠው ጉዳዩን የመታዘብ እና የማየት ፣ችግር ካላቸው ያን አስመዝግበው ወደፍርድ ቤት የሚሄዱ ከሆነም ያን አስመዝግበው ሰነዶቻቸውም ይዘው ክርክራቸውን የመቀጠል መሰረታዊ መብት አላቸው።

በዚህ ረገድ አብዛኛው ክልል ጥሩ የሚባል ሁኔታ አለ፤ ነገር ግን በሁለት ክልሎች (አማራ እና ደቡብ) በጣም አሳሰቢ በሆነ ደረጃ፣ በአንዱ (አፋር ክልል) በመለስተኛ ደረጀ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ መመልከቱን ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።

አማራ እና ደቡብ ክልሎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲ እጩ ወኪሎች ከቦታ ቦታ በፈለጉበት አግባብ መንቀሳቀስ እየቻሉ እንዳልሆነ፣ ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሆነ፣ ባጅ እየተቀሙ እንደሆነ ፣ ወደ ጣቢያ ሊጠጉ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ እጅግ በጣም ብዙ አቤቱታ ለቦርዱ ቀርቧል።

ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን መግለጫ ላይ የወሰድነው።