ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲከናወን መወሰኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በእለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምጻቸውን ለመስጠት ይችሉ ዘንድ እና የደምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር ይከናወን ዘንድ ቦርዱ የሚከተሉት ተግባራዊ እንዲሆኑ የምርጫ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/ 2011 አንቀጽ 161 የመተባበር ግዴታ መሰረት ለመንግስታዊ እና ለማንኛውም መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ያሳውቃል።

በዚህም መሰረት፣
– ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ የፌዴራል እና የክልል ( ከሃረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) መንግስታዊ ተቋማት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ስራ ዝግ እንዲያደርጉ

– ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ በክልሎች (ከሃረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) እና በፌዴራል የሚገኙ ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል ተቋማት በተመሳሳይ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዝግ እንዲያደርጉ እያሳወቀ

– የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የእለት ተእለት አገልግሎት ሰጪዎችም (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት..) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ የሚያከናውኑ ሲሆን የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም።

– የትራንስፓርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም ዜጎች ድምጽ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችን እና እቅዶችን እንዳይይዙ እና እንቅስቃሴያቸውን ድምጽ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ያበረታታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ