" /> በቡራዩ እና አካባቢው የደረሰው የህይወት መጥፋት በሌሎችም ቦታዎች እንዳይደገም መንግስት የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ሊያደርግ ይገባዋል | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

በቡራዩ እና አካባቢው የደረሰው የህይወት መጥፋት በሌሎችም ቦታዎች እንዳይደገም መንግስት የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ሊያደርግ ይገባዋል

  1. የፌዴራል ፖሊስና ሁሉም የጸጥታ ሃይሎች ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት በሰው ህይወት መጥፋት የተቆጣውን ህዝብ ድምጽ ከማፈን እና ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት ከመተኮስ ይልቅ ወዲያው የወንጀል ድርጊቶች እንደተፈጠሩና ከመፈጠራቸውም በፊት ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድና በየተወሰኑ ሰዓታት ጋዜጣዊ መግለጫዎች በመስጠት ህዝብ የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ መመሪያ እና ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል። የፌዴራል ፕሊስ የአመራር ጉድለት ለቡራዩ እልቂት ትልቅ አስተዋጻኦ ማድረጉ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ከዚህም አልፎ ፌደራል ፖሊስ 5 ዜጎችን በጥይት ገድሏል። ለዚህ የሰው ህይወት መጥፋት ተጠያቂ የሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል። ስህተቶቹ እንዳይደገሙ ከኮሚሽነሩ ጀምሮ የአመራርና የመመሪያ ለውጥ ያስፈልጋል።
  2. የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ማካከል ግጭት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ድርጊቶችና ቅስቀሳዎች እንዲቆጠቡ ሊመከሩና ሊገሰጹ ይገባል።
  3. የተጀመረውን ለውጥ ህብረተሰቡ እንዴት እንደሚያግዝና ወደሰላም፣ አንድነትና እና ልማት መንገድ ማምራት እንደሚቻል የሚጠቁሙና የሚያስተምሩ ተከታታይ የውይይት ፕሮግራሞችን ከሚዲያ ጋር በመተባበር ማካሄድ። ግጭቶች ሲከሰቱ ኢንተርኔት መዝጋት እና የህዝብ ድምጽ ማፈን ችግሮችን ማባባስ እንጂ መፍትሄ እንዳልሆነ አሁንም መንግስት የተማረ አይመስልም።
  4. ለሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት የፖለቲካ ፓርቲዎች የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳያካሂዱ ትብብራቸውን መጠየቅ።
  5. በቅርቡ ሲፈጸሙ ከቆዩት ግጭቶች ጀርባ ከፍተኛ መጠን ያለው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ፍሰት እንዳለ ይታወቃል። የዚህን ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምንጭ መመርመርና ተጠርጣሪዎቹን ለፍርድ ማቅረብ።
  6. በአሁኑ ወቅት ከ60 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብር የት እንዳለ ብሄራዊ ባንክ እና መንግስት እንዳማያውቅ ተነግሯል። ይህ ከመንግስትና ከባንክ እውቅና ውጭ ያለ ብር ከፊሉ በሃገሪቱ ውስጥ ግጭቶችን ለመቀስቀስና ለውጡን ለመቀልበስ ለሚደረገው ጥረት እየዋለ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ የብር ለውጥ እንዲያደርግ ያስፈልጋል።
  7. ከአንድ አመት ከ8 ወራት በኋላ ሊደረግ የታቀደውን ብሄራዊ ምርጫ ቢያንስ በሁለት ዓመታት ማራዘም ያስፈልጋል። የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስር ሳይሰድ እና ህብረተሰቡ ሳይረጋጋ ምርጫ ቢካሄድ ሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል። ምርጫ ከመደረጉ በፊት በቅድሚያ ህብረተሰቡ አመኔታ የሚጥልባቸው የህግ፣ የምርጫ፣ የሲቪክና የፖሊቲካ ተቋማት ሊገነቡ ያስፈልጋል። ለዚህም ቢያንስ ከ4 – 6 ዓመታት ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል ይገመታል።

የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV