ፌዴራል ፖሊስ የኦነግ አመራር አባላት የአቀባበል ሥነ ስርዓት በሰላም ተጠናቋል አለ።

የኦነግ አመራር አባላት የአቀባበል ሥነ ስርዓት በሰላም ተጠናቋል:-ፖሊስ

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች የተሳተፉበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት አቀባበል ሥነ ስርዓት በሰላም መጠናቀቁን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

መቀመጫውን ኤርትራ አድርጎ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ሲታገል የቆየው ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመወሰን ዛሬ አመራር አባላቱ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በአቀባበል ሥነ ስርዓቱ ላይ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ በርካታ ዜጎች በመስቀል አደባባይ ተገኝተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከትናንት ከዝግጅቱ ጀምሮ እስከ ዛሬ ፍጻሜው ድረስ የነበረው ሥነ ስርዓት እጅግ ሰላማዊ ነበር።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመከላከያ፣ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በትብብር በቂ ዝግጅት አድርገው እንደነበር ገልጸዋል።

ለመርሃ ግብሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቅ የአዲስ አበባ ወጣቶችና መላው ኅብረተሰቡ የነበረው ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች መርሀ ግብሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላሳዩት ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ኮሚሽኑ ከፍ ያለ ምስጋና እንዳለውምት ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ከትናንት ጀምሮ ለእንግዶች ምግብና ውሃ በማቅረብ ለፈጸሙት ቤተሰባዊ ተግባር ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ጉጂ፣ ታጠቅ፣ ቡራዩና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭትና ዝርፊያ የሚፈጽሙ ወሮበላና ወንበዴዎች እንዳሉ አረጋግጠናል ብለዋል።

ግጭቱና ዝርፊያው ከአቀባበል ሥነ ስርዓቱም ሆነ ከወጣቱ ጋር በማይገናኝ መልኩ የመንደር ወንበዴዎችና ዘራፊዎች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ እየተዘዋወሩ የፈጠሩት ችግር መሆኑን አስረድተዋል።

ፖሊስ ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።