“የመሪ ያለህ” የሚያስብሉ ብዙ ችግሮች ያሉበትን የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት መንግስት ሊያስተካክለው ይገባል።

ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር አሚር አማን (ጤና ጥበቃ ሚንስትር)፣ ሙያን ለባለሙያተኛ በዶክተር ኪያ ንጋቱ

ዶ/ር አብይ እና አጋሮቻቸው ወደሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን የለውጥ ንፋስ መንፈስ ጀምሯል። የለውጥ ንፋሱ የተቀማች ሀገራችንን ከማስመለስ ጀምሮ፣ በየመንግስት ተቋማቱ ተስፋ ሰጪ ለውጦች እንዲመጡ በር የከፈተ ጉዳይ ነው። የለውጥ ነፋሱ በእያንዳንዱ የመንግስት መዋቅር ውስጥ እጅግ ኋላቀር እና ጎታች የሆኑትን አሰራሮች ጠራርጎ መውሰድ እንደሚገባው እሙን ነው። እነዚህን ኋላቀር አሰራሮች ለራሳቸው ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ አልያም ከዕውቀት እና ለለውጥ ዝግጁ ባለመሆን ምክንያት እንዲቀጥሉ የሚፈልጉ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ቦታቸውን ብቃት ላላቸው ግለሰቦች በፈቃዳቸው በመልቀቅ እንቢ ካሉም ከለውጡ ባቡር ላይ ተገፍትረው መውረድ ይገባቸዋል።

እንደ አንድ ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጋም እነዚህን ክፍተቶች እና ክፍተቶቹ እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን በማጋለጥ፣ ገዚው ፓርቲ እንደሚለው “የማይተካ ሚናችንን መወጣት አለብን።” የመገናኛ ብዙሃንም፣ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ያሉትን ከፍተቶች በመንቀስ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አስተዋጸኦ ማድረግ ይገባቸዋል። ሀገራችን በልጽጋ በሁሉም መስክ ውጤታማ እንድትሆን በአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች ብቃት ከምንግዜውም በበለጠ ከፍተኛ መሆን፣ ለለውጥ መዘጋጀት፣ ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆን፣ አዳዲስ እና ዘመናዊ አሰራሮችን ለመከተል መሞከር፣ የሚሞክሩትንም በስራቸው ያሉ ሰራተኞች ለማበረታታት፣ የሠራተኞችን አቅም ከፍ ለማድረግ የሚተጉ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል። ይህ ከአንድ አመራር የሚጠበቅ መሰራታዊ ነገር ነው። እኔ በምሰራበት እና በቅርበት በማውቀው የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ውስጥ የዶ/ር አብይን ወደሥልጣን መምጣት ተከትሎ በሚስቴር ዴኤታነት ለጥቂት አመታት ያገለገሉት ዶ/ር አሚር አማን ወደሥልጣን መጥተዋል። ሚንስቴር ከሆኑም በኋላ በመስሪያ ቤቱ የተለያዩ የስራ ከፍሎች (ዳይሬክቶሬቶች) ላይ ይበል የሚይስብል የሥልጣን ሽግሽግ አድርገዋል።

ከዚህ ባሻገርም ከህብረተሰቡ ጋር ለመቀራረብ ያስችሎት ዘንድ በማህበራዊ ገጾች ለመገናኘት የሚያደርጉት ጥረት በብዙ ሰዎች ዘንድ እውቅናን አትርፎልዎታል። ከዚህም ባሻገር በየዳይሬክቶሬቶቹ አልፎ አልፎ በመሄድ ሰራተኞችን ለማበረታታት እና ቀለል ያሉ ሰው እንደሆኑ ለማሳየት የሚያደርጉትን ጥረት ሳላደንቅ አላልፍም። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ከፍተኛ ብቃት የሚጠይቁ አንዳንድ የሥራ ከፍሎች እስካሁን ድረስ “ከዕውቀት ነጻ” የሆኑ የፖለቲካ ሹመኞች ጉልት ሆነው እንዲቀጥሉ ያደረጉበት ምክንያት ለብዙዎች ግልጽ አይደለም። ይህ ግልጽ ደብዳቤም ለእርሶዎ በቀጥታ ሪፖርት ስለሚያደርገው ፣ በብዙዎች ዘንድም “የመሪ ያለህ” የሚያስብሉ ብዙ ችግሮች ያሉበትን የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬትን (ጤኢቴዳ/HITD) ይመለከታል። ጥቆማዬም እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ በሀገራችን ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከምትመኝ ግለሰብ በቅንነት የተደረገ፣ አላማው ማንንም ለማጥቃት እንዳልሆነ ተደርጎ እንዲወሰድልኝ አስቀድሜ ክቡርነትዎን እጠይቃለሁ።

የጤኢቴዳ/HITD ዳይሬክቶሬት ይህ ዳይሬክቶሬት በጤና ጥበቃ፣ በክልሎች እንዲሁም በተለያዩ የመንግስት ኤጀንሲዎች ሀገር አቀፍ የሆኑ የICT ሲስተሞችን፣ መተግበሪያዎችን፣ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን የሚመራ፣ የሚያስተባብር፣ የሚያበለጽግ እና ተግባራዊነቱን በመከታተል ግብረ መልስ የሚሰጥ ነው። ይህም ክፍል በህወሃት ካድሬ፣ ፈረንጆች iron fist በሚሉት መልኩ እየተመራ ያለ ክፍል ነው። ዳይሬክቶሬቱ በጣም በተደጋጋሚ አመታት ከአብዛኛዎቹ የሚንስቴሩ የስራ ክፍሎች ዝቅተኛውን የግምገማ ውጤት የሚያስመዘግብ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኋላቀር በሆነ “የአለቃ እና ምንዝር” አስተዳደር ስር እንደወደቀ ሳበስርዎ በታላቅ ሀዘን ነው። ይህ ክፍል ከኢትዮጵያ ጋር አቻ ከሆኑ ሀገሮች አንጻር የመረጃ ሥርዓትን ከመዘርጋት አንጻር በዳዴ የሚሄድ እንደሆነ ለመገንዘብ ሀገራቱን ሲጎበኙ አልያም የስራ ልምዳቸውን በሚያካፍሉባቸው ጉባዔዎች ላይ መገኘት እውነታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህም የሆነው ሰነፍ ወይንም ብቃት የሌላቸው ባለሙያዎች ስላሉ ሳይሆን ክፍሉን የሚመራው ግለሰብ የብቃት እና የአስተዳደር ክህሎት ችግር ስለሆነ ነው። አስተዳደራዊ ችግሮች በተጠቀሰው የስራ ክፍል ውስጥ የአስተዳደር ችግሮች ከመታየት አልፈው የሰራተኞችን የስራ ፍላጎት እና ሞራል እስከመስለብ የደረሱበት ሁኔታ ነው ያለው። ሃላፊው ደስ ባለው ስሜት ያለዕቅድ እና ግብ የሚመራ ብቃት የሌለው የፖለቲካ ሹመኛ ስለሆነ ነው።

የሰራተኞችን አቤቱታና ቅሬታ በማን አለብኝነት የሚደፈጥጥ፣ የሚያስፈራራ፣ የሚሳደብ እና ከስራ ውጤታማነት ይልቅ በወሬ እና በጥቅም የሚያምን ለቦታው ፈጽሞ የማይመጥን ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ የስራ ክፍሉ የተሰጠውን ግዴታ በአግባቡ እንዳይወጣ እንቅፋት እየሆነ ያለ፤ ዛሬ የተናገረውን ፈጽሞ በመካድ ነገ ላይ ፍጹም የተለየ አቋም በመያዝ፣ የተመቸውን ነገር በማን አለብኝነት እንደፈለገ የሚያደር ባለሙያዎች በብዙ ጥረት የሰሩትን ስራ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የልጆች ጨዋታ የሚያደርግ ግለሰብ ነው። ይህ ሰው ይሄንን ከፍተኛ ሃላፊነት የያዘው በስራ ብቃቱ እንዳልሆነ ለርሶ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት ነው የሚሆነው። ከእነማን ጋር ተወዳድሮ ለዚህ ሹመት እንደበቃ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። የዚያን ጊዜ የህወሃት የበላይነትን በመፍራት ወይንም በፖለቲካው ተቀባይነትን ለማኘት ታስቦ ሌሆን ይችላል፤ አሁን ላይ ግን ሀገራችንን በእውነት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስቡ ከሆነ ስህተቱን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው። “ብረትን መቀጥቀጥ በጋለ ጊዜ ነው” እንዲል ፈረንጅ። በዚህ የስራ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን በሀራችን ያሉ የጤና ተቋማት ያስተሳስራል ተብሎ የነበረው የVPN (HealthNet) ፕሮጀክት በበቂ ዕቅድ፣ ክትትልና ድጋፍ ባለማኘቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ተደራሽነት ከተጠበቀው እጅግ ያነሰ መሆኑ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስኬጃ ጤና ጥበቃ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለኢትዮ ቴሌኮም የከፈለ ሲሆን ስምምነቱ በዶ/ር ደብረፅዮን ጊዜ የተፈጸመ እና ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሞበታል እየተባለ የሚታማ ነው።

ያው ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው በሚል ነው እንጂ እርስዎም ይህንን ሀሜት ሳይሰሙ አይቀርም። ሀሜትን ካነሳን አንጻር ግለሰቡ በቅርቡ ባልተለመደ መልኩ ከለውጡ በኋላ ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተጓዘ ሲሆን በሄደባቸው አካባቢዎች በሳምንት ወይንም በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ተከስተዋል። ሀሜት አቅራቢዎችም እንደ ማሳያ ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ይጠቅሳሉ። በተላላኪነት፣ ገንዘብ አቀባይነትም ይወነጀላል። ሀገር አቀፍ የሆነውን የጤና ስርዓታችንን የሚያሳልጥልንን የDHIS 2 ትግበራ ያለበቂ ዕቅድ ወደትግበራ እንዲገባ እና የVPN ዝርጋታው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ሀገራችንን ለከፍተኛ ወጪ እና የሀብት ብክነት ያስገባ የትግበራ ስልት እንድትከተል ሆኗል። ይህ በአጭር ጊዜ መመለስ የሚያስቸግር ጉዳይ ቢሆንም ለተቀሩት ስራዎች ከፍተኛ ትምህርት መስጠት አለበት። እርስዎም ትግበራውን በቅርብ የሚከታተል ቡድን አቋቁመው ክትትል ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ። እግረ-መንገድዎንም በታችኛው የጤና መዋቅር ላይ ተተግብሮ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ስራ በማቀላጠፍ ህብረተሰባችን ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው eCHIS የኤሌክትሮኒስክ ሲስተም በአመራሩ ምክንያት የግለሰቦች መጫወቻ እና መለማመጃ ስለሆነ ክትትልዎ አይለየው። እሺ፣ ምን ይደረግ? በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ የሀገሪቱን የጤና መረጃ ስርዓት ይመራል ተብሎ በሚጠበቅ ክፍል ውስጥ ሰር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የመጀመሪያው ሂደት አሁን ያለውን አመራር ማስወገድ ነው።

ይህ እንግዲህ የመፍትሄው የመጀመሪያ ሂደት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። ጥገናዊ ለውጥ “ሀምሌ ቢያባራ በጋ ይመስላል” የሚለውን አባባል ከማስታወስ በቀር የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ አስረግጬ ልነግርዎ እወዳለሁ። ይህንን ስር ነቀል ለውጥ ሁሉም ሰራተኛ በሙሉ ልቡ እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነኝ። ሀገሪቷ በፈጣን የለውጥ ባቡር ወደፊት እየተምዘገዘገች ባለበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት ካድሬዎችን እያራገፉ በብቁ ባለሙያዎች መተካት ካልተቻለ በዕቅድ የተያዘውን የኢንፎርሜሽን ሬቮሉሽን ውጤታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ “ላሊበላ ሄደሽ ክህንጻው ብትሰፍሪ፣ አይገኝም ጽድቅ አለ ባህሪ” የሚለውን ተረት እንድተርት ያስገድደኛል። ስለሆነም የስራ ክፍሉን በብቁ ባለሙያ እንዲተዳደር ማድረግ ተገቢ ነው። የሚሾመው ባለሙያ የሄልዝ ኢንፎርማቲክስ ዕውቀትን የያዘ እና በቂ የስራ ልምድ ያለው ቢሆን ተመራጭ ነው እላለሁ። ከዚህ ባሻገር አሁን እንዳለው አመራር የስነ ምግባር ችግር የሌለበት፣ ሁሉንም ሰራተኞች እኩል የሜያይ፣ ሰርቶ የሚያሰራ፣ የእሳት ማጥፋት ስራ ሳይሆን በዕቅድ የሚመራ፣ ከሌሎች የሰራ ክፍሎች ጋር ጤናማ ግኑኝነት መፍጠር የሚችል ቢሆን ለውጡን በአጭር ጊዜ ማየት ይቻላል። ስለሆነም ይህንን ጥቆማ በማየት ዶ/ር አሚር አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳሉ ብዬ አምናለሁ።