ኢድ አልፈጥር – የረመዳን ፆምን ማብቃት የሚያበስረው በአል

በእስልምና ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ ሁለት ኢዶች (በአሎች) አሉ፡፡ የመጀመሪያው የረመዳን ፆምን ማብቃት የሚያበስረው ኢድ – አልፈጥር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደሞ ከሁለት ወራት በኋላ የሐጂ ስነ – ስርዓትን ተከትሎ የሚመጣው ኢድ – አልአድሓ (የእርድ በዓል ነው፡፡ ረመዳን ተጠናቆ የምናከብረው በዓል ኢድ አልፈጥር) ስለሆነ እኔም የማወራችሁ ስለዚሁ ክብረበዓል አጠቃላይ ገፅታ ነው፡፡

ረመዳን፤ ሙስሊም ምእመናን ራሳቸውን የሚያንፁበት፣ ወደ አምላክ የሚቀርቡበት የኢማን እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ የፆም ወር ነው። የረመዳን ወር ከሌሎቹ ወራቶች የተለየና ትልቅ የሚያደርገው፣ ምእመናን ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት አንስቶ እስከ ጠለቀችበት ድረስ ከምግብ፣ ከውሐ፣ ከወሲብ ግንኙነት (ህጋዊ ትዳርን ጨምሮ)፣ ከመጥፎ ንግግር እና ባህሪ የተቆጠቡ መሆን ስላለባቸው ነው፡፡ በእርግጥ ህጋዊ ያልሆነ ወሲብን ጨምሮ ሌሎቹ መጥፎ ባህሪያት በሌላው ወር ይፈቀዳል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የወሩን ታላቅነት አፅንኦት ለመስጠት አላህ የደነገጋቸው ህጎቹ ናቸው። በተጨማሪም 30 ጁዝ (ምዕራፍ) የያዘውን ቅዱስ ቁርአንን ምዕመናን በረመዳን አንብበው የሚያጠናቅቁበት ወር ነው፡፡

የረመዳንን ወር ከአንድ አነስተኛ የማሰልጠኛ ተቋም ጋር ማመሳሰል እንችላለን፡፡ በአንድ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሆነ ዘርፍ አጥንተን እውቀትና ስነ – ምግባሮች እንደምንጨብጠው ሁሉ፤ በረመዳን ወቅትም በቁርአን እውቀት አዕምሯችንን አበልፅገን፣ በመንፈሳዊ እሴቶች ተሐድሶ ወስደን የምንወጣበት ወር ነው፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ሰልጣኞች አካላቸውን ለማፈርጠም እና የሰውነታቸውን ጥንካሬ ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱት ሁሉ፤ በረመዳንም ምእመናን መንፈሳዊ ጥንካሬን ለማግኘት እምነቱ የሚያዘውን አመጋገብ ዘይቤ ይለውጣሉ፡፡ እንዲሁም በረመዳን ወር ብቻ የሚገኙ ሃይማኖታዊ ስልጠናዎችን ተግብረው ቀሪውን ህይወታቸውን ከፈጣሪ ጋር ለማቀራረብ ይሞክራሉ፡፡ በጎ ስራዎችን ማሳደግ እና የአምልኮ ስርአቶችን በብዙ መፈፀም ሌሎቹ የስልጠና ግብአቶች ናቸው፡፡

ራሳችንን ከምግብና ከውሃ ማቀብ፣ በድህነት ለሚኖሩ ሚስኪኖች እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ምግብና ውሃ አጥቶ መኖር ምን እንደሚመስል የምናውቀው በረመዳን ወር ነው፡፡ ምግብና ውሃ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቅንጦት ነገሮችን ማጣት ያለውን ስሜት በረመዳን ወር ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ራስን ዝቅ አደርጎ ለፈጣሪ መስገድ ያለውን እርካታ ረመዳን ይነግረናል፡፡ ማፍጠሪያ ሰዓት ደርሶ ከቤተሰብ እና ከወዳጆች ጋር ተሰብስቦ አብሮ መብላት ራሱን የቻለ የማህበራዊ በጎ እሴት ነው፡፡ ከነዚህ ስልጠናዎች በኋላ የሚቀረን ተመርቆ ከስልጠናው መሰናበት ነው፡፡ የረመዳን ምረቃ ደግሞ ኢድ – አልፈጥር ነው። ምእመናን ኢድ – አልፈጥርን በማክበር ከረመዳን ስልጠናዎች ተመርቀው ይወጣሉ፡፡

ኢድ – አልፈጥር ትርጉሙ ራሱ የፆም ማጠናቀቂያ ክብረ – በአል እንደማለት ነው፡፡ በአብዛኛው “የአለም ሀገሮች ውስጥ ለ3 ቀናት በድምቀት ይከበራል፡፡
ኢድ አልፈጥር በብዙ ሀገሮች በተለያዩ መንገዶች ቢከበርም የጋራ የሆነ አንድ ነገርን ይዟል፡፡ ይሄውም በበአሉ ቀን ሁሉም አማኞች በጧት ተነስተው ልዩ የሶላት ስግደት ወደሚደረግበት ቦታ ይተማሉ። በኛ ሀገር ምእመናን በለሊት 11 ሰዓት ተነስተው ወደ ስግደት ከመሄዳቸው በፊት ተሰብስበው ገንፎ በቅቤ ወይም በተልባ ይበላሉ፡፡ አሁን አሁን ብዙም ባይስተዋልም እንጀራ በፌጦ የመጉረስ ልማድ ነበር። (በሀገራችን ለዘመን መለወጫ መስከረም ላይ እንደሚደረገው አይነት)
የኢድ-አልፈጥር ስግደት የሚደረገው በመስጂድ ውስጥ ወይም ሁሉንም አማኝ ሊያሰባስብ በሚችል አንድ ገላጣ ቦታ ላይ ነው፡፡ የእምነቱ ተከታዮች በቡድን እየሆኑ ተክቢራ በማድረግ (የበአሉ የውዳሴ ዜማዎች) ወደ ስግደቱ ቦታ ይተማሉ፡፡ በሀገራችን ውስጥ ሙስሊሞች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቡድን እየሆኑ፣ ተክቢራ እያደረጉ ወደ ስታዲየም እንደሚሄዱት ማለት ነው፡፡

ከስግደት መልስ ምእመናን የበአል ድግስ አድርገው ከቤተሰብ፣ ከዘመድ – አዝማድ እንዲሁም ከጐረቤት ጋር በአሉን በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ ቤተ ዘመዶችን እየዞሩ መጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ ማለት የኢድ አልፈጥር ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የምግቡ አይነት እንደየባህሉ ከሀገር ሐገር ቢለያይም፣ ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀት ግን የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይ ህፃናቶች በኢድ አልፈጥር ጊዜ በአዲስ ልብሶች አጊጠው በዘመድ አዝማድ ቤቶች እየዞሩ “የሚናኢድ” በማለት ሳንቲሞችን ይቀበላሉ፡፡ ይህ በአል በህፃናቶች ዘንድ ልዩ በመሆኑ ከቤተሰብና ከዘመድ አዝማድ የሚሰበሰቡት ሳንቲሞች በጣም ብዙ ናቸው፡፡

አንድ ሙስሊም በረመዳን ማፍጠሪያ ወቅት ምጽዋት ያልሰጠ ከሆነ የኢድ አልፈጥርን በአል ተጠቅሞ ለሚስኪኖች ዞካ መስጠት አለበት፡፡ የምግብ አልያም የገንዘብ ስጦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች የበአል ድግስ አድርገው ደሐዎችን ያበላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የታረዙትን ያለብሳሉ፡፡ ምንም ይሁን ነገር ግን በኢድ አልፈጥር በአል ወቅት ለድሐዎች የምጽዋት እጆችን መዘርጋት ሐይማኖቱ የሚመክረው በጐ ተግባር ነው፡፡ መልካም የኢድ አልፈጥር በአል ለመላው የእስልምና ተከታዮች በሙሉ እንዲሆን እየተመኘሁ እሰናበታለሁ፡፡

Source Addis Admass