በግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅታለች !

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ውይይት ስለማድረጋቸው ተገልፆ ነበር።

ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ውይይቱን የተመለከተ መረጃ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት እና በአፍሪካ ሕብረት መራሹ የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ከአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን እና ከልዑካቸው ጋር ግልፅ የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልፀዋል።

ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ፥ አባይን መጠቀም ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እና ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመልዕክተኛው ማስረዳታቸውን ነው አሳውቀዋል።

አምባሳደር ፌልትማን ሦስቱ ሀገሮች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት የሀገራቸውን ቅንና ገለልተኛ ድጋፍ እንዲሁም ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ሲሉ አብራርተዋል።

ፊልትማን በሱዳን በነበራቸው ቆይታ ወቅት በህዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

ሶስቱ ተደራዳሪ ሀገራት ካልፈቀዱ በስተቀር አሜሪካ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡

በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ የሚገኙት ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎችም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።