አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላትን አይሳካላችሁም አሉ

ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚያሴሩ አካላት ያሰቡት በፍጹም ሊሳካላቸው እንደማይችል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪና የምርጫ ጉዳይ ደህንነትና ጸጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ።

ምርጫውን ለማደናቀፍ የዐመፅ ፍላጎት ያላቸው አካላት አቅደው እየሠሩ ቢሆንም የዚህ ምርጫ ዋነኛ ባለድርሻ በሆነው በኅብረተሰቡ፣ በፌዴራልና በክልል ጸጥታ ኃይሎች ንቁ ሕግን የማስከበር ሥራ ህልማቸው አይሳካም ብለዋል።

የአሁኑ የኢትዮጵያ ምርጫ በሽግግር ሂደት ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በመሆኑ አንዳንድ የጸጥታ እንቅፋቶች ሊያገጥሙ እንደሚችሉ ያመለከቱት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የመንግሥት አጠቃላይ ግምገማ የሚያመላክተው ከሀገሪቱ ስፋትና የምርጫ ሰፊ ዝግጅት አንጻር የጸጥታ ችግር የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ተጽዕኖ የከፋ እንደማይሆን ጠቁመዋል።

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በወለጋ አራት ዞኖች ባሉ የተወሰኑ ወረዳዎች፣ በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች እና በደቡብ ክልልም የተወሰኑ አካበቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች እንዳሉ አስታውሰዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ መንግሥት ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ጸጥታን ለማስከበር ዕርምጃ እየወሰደ በመሆኑ ከአጠቃላይ ምርጫው ሂደት አንጻር ተጽእኗቸው ዝቅተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።