የውሸት መረጃ ነው ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ በሱዳን ኃይሎች ላይ አንዳችም የአፀፋ እርምጃ አልወሰደም ፤ ቦታዎቹን የሱዳን ኃይሎች እንደያዙት ነው

“ይሄ የውሸት መረጃ ነው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ አንዳችም የአፀፋ እርምጃ አልወሰደም” – አቶ ተስፋሁን ሲሳይ

ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ “የኢትዮጵያ መከላከያ በሱዳን ኃይሎች የተያዘውን ቦታ አስለቀቅ፤ ሱዳኖቹም አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል” የሚሉ የተለያዩ ወሬዎች ሲሰራጩ ነበር።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ሲሳይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚወራው ሀሰት መሆኑ ለቢቢሲ ሬድዮ የትላንት ስርጭት ተናገረዋል።

የሱዳን ኃይል ከዚህ ቀደም የያዘውን አካባቢዎች አሁንም ለቆ አልወጣም ብለዋል።

አቶ ተስፋሁን፥ “አሁን ባለው ሁኔታ ምንም አይነት ግጭት የለም፤ አሁንም ቦታዎቹን እነሱ እንደያዙት ነው ያለው፤ የተለየ የተደረገ እንቅስቃሴ የለም በኢትዮጵያ በኩል” ሲሉ ተደምጠዋል።

በአካባቢው የመከላከያ እና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች ስለመኖራቸው እና የወሰዱት የአፀፋ እርምጃ/ቦታዎቹን ለማስለቀቅ ያደረጉት ጥረት እንዳለ የተጠየቁት አቶ ተስፋሁን ፦ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች መኖራቸውን ገልፀው እስካሁን ቦታውን ለማስለቀቅ ያደረጉት ጥረት እንደሌለ /የአፀፋ እርምጃም እንዳልተወሰደ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጦር እርምጃ ወስዶ የሱዳን ኃይል የያዘውን ቦታ ለቆ ወጥቷል ተብሎ የሚወራውን ጉዳይም አቶ ተስፋሁን ፥ “ይሄ የውሸት መረጃ ነው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ አንዳችም የአፀፋ እርምጃ አልወሰደም ፤ ያደረገም ነገር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ አንድ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ፥ አሁንም የተያዘው መሬት በሱዳን እጅ እንዳለ ገልፀዋል። “እስካሁን መፍትሄ ሳይገኝ ክረምት ገብቷል፤ ለማረስም አይታሰብም፤ ተስፋ ቆርጠን ያለን የሌለን ንብረት አጥተን ነው ቁጭ ብለን ያለነው” ብለዋል።

ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል/የተፈናቃዮች ሁኔታስ ?

የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ፥ “በባለፈው የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ የቆዩ። አልፎ አልፎ ፤ በወር አንድ ቀን ፣ በ2 ሳምንት አንድ ቀን ካምፕ የማቃጠል ነገር አለ ፣ከርቀት የመተኮስ ነገር አለ፤ ይሄ አልፎ አልፎ ከሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ነው ያለው። በነሱ በኩል ያን ያህል የተደራጀ እንቅስቃሴ የለም። ነገር ግን ባለፈው የያዙት ቦታ ያቃጠሏቸው የባለሃብት ካምፖች ፤ አሁንም በነሱ ቁጥጥር ስር ነው ያለው፤ ባለሃብቶችም ለማረስ ተቸግረዋል”

ምንጭ፦ ቢቢሲ