በሐገሪቱ ያለው የሰላም እጦት የመንግስት የጸጥታ ተቋማትን ክሽፈት ያመለክታል።

ግዴታውን የሚወጣ ታክስ የሚከፍለው ሕዝብ ለመብቱ የሚቆምለትን መንግስት እንጂ በመብቱ ላይ የሚቆምበትን መንግስት አይፈልግም።ሕዝብም ከመንግስት የሚጣልበትን ግዴታ እንደሚወጣ ሁሉ መብቱንም የመጠየቅ ግዴታ አለበት ችግሮች በተነሱ ሰዓት ሁሉ ከመጠቋቆም ይልቅ ስር ነቀል መፍትሔ መፈለግ የመንግስት ዋነኛ ስራ ሊሆን ይገባል።

ምንሊክ ሳልሳዊ — የመንግስት የፀጥታ ተቋማት ለሀገር ሰላምና ደሕንነት ትልቁንና ቀዳሚውን አስታውፆ የማበርከት ግዴታ አለባቸው። ሕዝብ ታክስ የሚከፍለው አንዱና ዋነኛው የሆነውን የመንግስትን ተቋማቶች ለመገንባትና ተግባራዊ የፀጥታ ስራዎችን እንዲሰሩ በማገዝ ሰላሙንና ደሕንነቱን እንዲጠብቁለት ነው። ሕዝብ በመንግስት ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን በራሱም ተነሳሽነት ተጨምሮበት ግብር የሚከፍለው በሰላም ወጥቶ ለመግባት፣ የመኖር ሕልውናውንና የመስራት መብቶቹ እንዲከበሩለት የመንግስትን ጥበቃና አገልግሎቶችን ለማግኘት ካለው ብርቱ ምኞት የመነጨ ነው።

መንስትም የሕዝብን ግብር ታክስ እስከሰበሰበ ድረስ የሕዝብን ጥያቄዎች የመመለስ ኃላፊነት አለበት። ሕዝብ ግዴታውን ሲወጣ መንግስትም የሕዝብ መብቶች እንዲከበሩ አስተዳደራዊ መስእዋትነት ሊከፍል ግዴታ አለበት። የመንግስት የስራ ድርሻ እንደ ደሕንነትና ፖሊስ የመሳሰሉትን ተቋማት በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በመስራት ለሕዝብ የቆሙ ተቋማትን መገንባትና ሕዝብን ማገልገል ነው።

ግዴታውን የሚወጣ ሕዝብ ለመብቱ የሚቆምለትን መንግስት እንጂ በመብቱ ላይ የሚቆምበትን መንግስት አይፈልግም። ይህንን ደግሞ መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። መንግስት በመዋቅሮቹ ውስጥ ያሉትን እኩይ አስተዳደራዊ ሰንኮፎች እግር በእግር እየተከታተለ መንቀል ግዴታው ነው። ከሙስና ጀምሮ እስከ መብት ገፈፋ፣ ከግድያ ጀምሮ እስከ ማፈናቀል የሚካሔዱ እኩይ ተግባራት ጀርባ ያሉ ባለስልጣናቱን በመንቀል ለሕዝብ ሊያገለግሉ የሚችሉ አስተዳዳሪዎች ማስቀመጥ ያለበት መንግስት የጸጥታ ኃይሉን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት አለበት።

የደሕንነትና የፖሊስ ተቋማት በየክልሉ የሰላም መደፍረሶችን ለመቆጣጠርና ለማክሸፍ ቀድመው ቢገኙ ኖሮ በመረጃና በሎጀስቲክ ተዘጋጅተው በቦታው ቢደርሱና በየአከባቢው ያለውን የጸጥታ ተቋም ቢያዋቅሩና መረጃዎችን ሰብስበው ወደ ተግባር ቢቀይሩ ኖሮ ይህ ሁሉ አደጋ ባልተከሰተ ነበር። በሐገሪቱ ያለው የሰላም እጦት የመንግስት የጸጥታ ተቋማትን ክሽፈት ያመለክታል።

መንግስት የደሕንነት ተቋማቱንና የፖሊስ ኃይሉን ክፍሎች ሊፈትሽ ይገባል። ተቋማቱ ሊከለሱ ድጋሚ ሊደራጁ በጽኑ የማይለወጥ አቋም ሊገነቡ እንደሚገባ ከማወቅም በላይ በየክልሉ ያሉትን የጸጥታ መዋቅሮች በስሩ አድርጎ በአንድ አመራር በማደራጀት ከሚመጡ አደጋዎች ሕዝብን ሊጠብቅ ይገባል። ግብር ከፋዩን ሕዝብ የመጠበቅ ግዴታ የመንግስት ነው።ለፖለቲካ ፍጆታና ለስልጣን መደላደል መሮጥ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች መሰረታዊ የመኖር ሕልውናና መብት መስራትም ትልቅ ድል ያቀዳጃል። #MinilikSalsawi