ሕዝብን ተሸናፊ የሚያደርግ ፖለቲካ ይወገድ

ሕዝብን ተሸናፊ የሚያደርግ ፖለቲካ ይወገድ!ሲራራ – Sirara


ፖለቲካችንን አርአያነት የለውም፡፡ ከኀልዮት፣ ከመርህና ርዕዮት ይልቅ በደመነፍስ፣ በጥቅመኝነትና በጉልበት የሚነዳ ነው፡፡ በሕዝብና በአገር ስም ሕዝብና አገርን የሚያወድም፣ ከእኔ በላይ ላሳር ገመድ የተተበተበ ግትር ነው፡፡ ስለዚህም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ አቻችሎ ከመኖሪያነት ይልቅ፣ አለቅጥ አካርሮ የአጥፍቶ መጥፋት ቀለበት ውስጥ ተቀርቅሯል፡፡ በቀላሉ የፖለቲካ ተፈጥሮውን አጥቶ፣ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ሆኗል፡፡ ዛሬ ብሔራዊ ህልውናችን የተንጠለጠለው በዕድገትና በልማት፣ በፍትሕና በእኩልነት ወይም በዴሞክራሲና ሌሎች ለሕዝባችን መሠረታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ አይደለም፡፡ እነዚህ ላይደማመጡ በተማማሉና ደም በተቃቡ፣ አገራቸውን ከራሳቸው ጋር ከርሰ መቃብር ለመክተት በቆረጡ የልኂቃን አንጃዎች አንደበት አፍ የቅንጦት ቃላት ናቸው፡፡

ሕዝባችንን ከረኀብና እርዛት፣ ከፍትሕና ርትዕ እጦት፣ ከበይ ተመልካችነትና የጥቂቶች ሎሌነት የሚታደገው አልተገኘም፡፡ ጥቂት ግለሰቦች በታሪክ አጋጣሚም፣ በነፍጥም፣ በጎሳም፣ በዝምድናም ሆነ በጥቅም ተቧድነው ሥልጣን የሚጠቀልሉበትና በሕዝብ ስም ሕዝብ ላይ የሚቀልዱበት አዙሪት አላበቃም፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከነሱ የተሻለ ርዕይ ያለ አይመስላቸውም፡፡ የልማት ሐዋርያት፣ የሰላም ጠበቆች፣ የሕዳሴ ደቀመዛሙርት፣ የጥበብ ሁሉ መፍለቂያ ናቸው፡፡ ሕዝብ ደግሞ የፈረደበት ግዑዝ እና ቤተ ሙከራ ነው፡፡ ዝምታው ድንቁርና፣ ሆደሰፊነቱ ቂልነት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዓመታት በብረት አለንጋ ሲገረፍ ሰጥ ለጥ ማለቱ፣ ለታጠቀ ገባሪ፣ ፊት አይቶና ተመጽውቶ አዳሪ እንዲሆን የተገደደው አቅም በማጣቱ ነው፡፡ አምሳለ ሰው ከሰውነት ተርታ በሚያወርድ ዘውግ በሚለካበት፣ ሰብአዊነቱ ጭምር በሌሎች መልካም ፈቃድ ሥር በወደቀበት፣ ማኅበራዊ ህልውናው በስጋትና በጥርጣሬ በተቀፈደደበት፣ ሕዝብ ከሕዝብና ከመንግሥት መተማመን በጠፋበት ሁኔታ ማኅበራዊ ሰላም ከቶም ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ሰላሙን አጥቶ ሰላማዊ በመምሰል ይገበዛል፡፡ በእዝነ ልቡናው መራራ ቁጭት አግቶ፣ በቀቢፀ ተስፋ ፍዳውን ይቆጥራል፡፡

“እውነት ይህቺ የእኔ አገር ናት?”፣ “ምን አገር አለኝና!”፣ “የት ተሂዶ ይኖራል?”፣ ወዘተ… የሚሉ ነገሮችን በየአደባባዩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከዚህ ሲኦል አፋፍ የደረስነው በዘመናት በትውልዶች ጫንቃ ተረማምደን ነው፡፡ አገርን ከብሔር፣ ሕዝብን ከሕዝብ አቃቅረን፣ ድልድዮቻችንን አፍርሰን፣ መተሳሰሪያ ድሮቻችንን በጣጥሰን ነው፡፡ እልፍ ሚሊዮኖችን በችጋር ቆልተን፣ በልበ ድንጋይነት ምንተሺሕ ገብረን፣ በእናቶቻችን እምባ፣ በወንድሞቻችን የደም ጎርፍ ታጥበን ነው፡፡

ጉዳዩ ረዘም ያለ ታሪካዊ ሥር ቢኖረውም ቅሉ፣ የብሔር ፖለቲካን የህልውናው አስኳል በማድረግ የፍልሚያውን መስመሮች በማያሻማ ሁኔታ የወሰነው ዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ከለውጥ በኋላ ያለውም ሁኔታ እምብዛም አልተለወጠም፡፡ በዓለም አምሳያ የሌለው ብሎ የሚመጻደቅበት የማንነት ፖለቲካ ሕዝቦችን ከእርስ በርስ መጠራጠር፣ ጥላቻና ግጭት አርቆ ሰላምና ፍቅር አላመጣም፡፡ አገሪቱን ከእርስ በርስ መጠፋፋትና መበታተን አደጋ መታደግ አልቻለም፡፡

ይህም መንግሥት ዘውገኝነት አፍራሽ አመለካከት መሆኑን ሊገነዘብ አልቻለም ወይም አልፈለገም፤ ቢያንስ በራሱ ህልውና እስኪመጣበት ድረስ፡፡ ዘውገኝነት በከፊል ከፍርሃትና ከእምነት ማጣት የሚመነጭ ሥነ ልቡና ነው፡፡ ስለዚህም ዘውገኝነት በመለዘብ ፋንታ እየገረረ ከሄደ፣ መንግሥት አስተማማኝ ዋስትና ሊሰጥና በማኅበረሰቦች መካከል መፈራራት እንዲከስም፣ መተማመን እንዲጎለብት ማድረግ አቅቶታል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ መንግሥታዊ የዘውገኝነት ፖለቲካ፣ ኅብረ ብሔራዊነት፣ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት የተባሉትን አቋሞች ሊያጠፋ ቀርቶ ሊያከስምም አልቻለም፡፡ አንዱን አራግቦ ሌላውን የመግደል መንገድ የለምና፡፡ በዘውግና በባሕል መስመር የተደራጁ ፓርቲዎችን አቅፎና ደግፎ፣ በፖለቲካና በርዕዮተዓለም የተሰባሰቡትን ማሳደድና ማጥፋት አላዋጣም፡፡ ብዝሃነትን ከኢትዮጵያዊነት በተቃርኖ ማሳለፍ፣ ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ፣ ትዕምርት፣ ታሪክ፣ ቅርስ መካድና ማዋረድ ቀድሞውንም አጀንዳው ሌላ ነው፡፡

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው፣ ጉዳዩ ሆነ ተብሎ በአንድ ቃል ታስሮ በመድበስበሱ እንጂ፣ ብዝሃዊነት “በኅብረ ባሕላዊነት” (multiculturalism) ይገለጻል፡፡ የኅብረ ባሕላዊነት ፍልስፍና ሰፊና ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ሥነልቡናዊ፣ ወዘተ… ጎኖችን ያካትታል፡፡ ለኅብረ ባሕላዊነት፣ ባሕሎች ያፈጁ፣ ዝጎችና ሙቶች ሳይሆኑ፤ ታዳሸ፣ ክፍቶችና ህያዋን ናቸው፡፡ የኅብረ ባሕላዊነት ቁልፍ እሳቤ መነጠልና በራስ መዋጥ ሳይሆን፣ ብዝሃዊነትን ተገንዝቦ በማኅበረሰቦች መካከል መስተጋብርን መፍጠር መቻል ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ኅብረ ባሕላዊነት ማለት ብዝሃነት በአንድነት ውስጥ የሚስተናገድበት ሚዛናዊ ቀመር ነው፡፡ ስለሆነም የሕዝቦችን ግላዊ ማንነት የማያከብር፣ በመቀራረብና መተዋወቅ ፈንታ መራራቅንና ባይተዋርነትን የሚያራግብ፣ ሰፊ የተራክቦ መንገዶችንና ዕድሎችን ከመዘርጋት ይልቅ በጠባብ ፖለቲካዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ብዝሃነትም ይባል አንድነት አገር አፍራሽ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሠራሹ ጎራ የሚራመደው ፖለቲካ አደገኝነቱ በብዝሃነት ሽፋን ጎሰኝነትንና ዘውገኝነትን ስለሚያራምድ ነው፡፡ ብዝሃነት የሚፈልገውን ቁልፍ ኅብረ ባሕላዊ ዳያሎግ ወደተራ ስብከትና ቅስቀሳ ስለቀየረው ነው፡፡ ሥርዓቱ ለብዝሃነት የቆምኩ ነኝ ቢልም፣ በተግባር ግን በአንድ አስተሳሰብ የቆረበ፣ ሌሎች አማራጮችን ለማዳመጥ እንኳን ትዕግስት የነሳው በአሃዳዊ አመለካከት የሚመራ መንግሥት ነው፡፡

ዛሬ ህልውናችንን እየተፈታተኑን ያሉት ፍጹም ተጻራሪ ጎራዎች ሊሸናነፉ የሚችሉባቸው መንገዶች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ አንደኛውና ሰላማዊው አዛላቂ መንገድ በፍትሐዊና ሐቀኛ ምርጫ ነው፡፡ ይህ መንገድ ዝግ ይመስላል፡፡ በሁለቱ ጽንፎች መካከል ያሉት ሰፊና አቻቻይ አማራጮች ዕድል ተነፍገዋል፡፡ አቻቻይነት እንደ መሃል ሰፋሪነት፣ ለዘብተኝነት እንደ አድርባይነት የሚቆጠርበት የፖለቲካ ባሕል ነግሷል፡፡ ስለዚህም ሁለተኛውና የአመፁ መንገድ ደግሞ በጦር ኀይል አሸንፎ ፍላጎትን በጉልበት መጫን፣ ወይም የአመለካከቱን አራማጆች ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው፡፡ በታሪክ በርካታ ጊዜ ተሞክሯል፣ ግን አልተሳካም፡፡ ይሁዲዎችን ማቃጠል ለይሁዳዊነት “የማያዳግም መፍትሔ” አልሆነም፡፡ ቱትሲዎችን በመጨፍጨፍ ሩዋንዳን የኹቱዎች ብቻ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በኀይል የሚፀና፣ በብረትና በእቶን የሚገርፍ ሥርዓት መካረርን፣ በቀልና ደም መፋሰስን መጋበዙ አይቀሬ ነው፡፡

አገራችን የቆመችው ከሰላም ወደ ኀይል በሚወስደው መስቀልያ መንገድ ላይ መሆኑን መጠራጠር የዋህነት ነው፡፡ ከፊታችን የተደቀነው ሰቆቃና ጨለማ ግዘፍ እየነሳ መጥቷል፡፡ አያድርገውና ይህ ቢከሰት የሚጎዳው አንድ ወይም የተወሰነ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁላችንም እንደ ሕዝብና እንደ አገር ነው፡፡ ከእንዲህ ያለው መዓት አገራችን በአንዳች ተዓምር ብትተርፍ ምን እንደምትመስል መገመት ያዳግታል፡፡ የፈለገው ቢሆን ግን፣ ሕይወት እስካለች ድረስ ተስፋ ማድረግ ይገባል፡፡ በእነዚህ አጥፍቶ ለመጥፋት በተሰላለፉ ጎራዎች መካከል ከክር የቀጠነች ድልድይ መፍጠር ቢቻል እንኳን ብለን ለማሰብ እንገደዳለን፡፡ ይህ ደግሞ እንዲፈጠር መጀመሪያ ፖለቲከኞቻችንን ከእውነታው ማጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡

ዕድሜ ልካቸውን ያዳወሩት የውሸት ምናባዊ ዓለም ከራሳቸው አልፎ በተጨባጭ ለሕዝብና ለአገር ያስገኘው ትሩፋት እንደሌለ እንዲያውቁት ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ሕዝባችን ከመቼውም በከፋ ሰላም የራቀውና ችጋር ያደቀቀው በነሱ የሰርክ አፍለኛ ፖለቲካ መሆኑን ማስጨበጥ ያሻል፡፡ አይሆንም እንጅ ቢሆን፣ “እኔ ከሞትኩ” ከሚባለው ደመነፍሳዊና ዘይቤ ተላቅቀው፣ ኀልዮታዊና ታሪካዊ አድማስ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥንቱንም ታሪካቸውን ቢያከብሩና በታሪክ ተጠያቂ መሆንን ቢፈሩ ከዚህ የድፍረትና ማናለብኝነት አረንቋ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ባልዘፈቁ፡፡ የልጆቻቸውን ዓለምና እጣ ጭምር ለመቆመር ባልሞከሩ፡፡

ይህም ቢሆን የተፈጥሮ ሕግ አይሻርምና አሮጌው መሄዱና አዲሱ መተካቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማሰብ ያለብን ካፈጀው የአመለካከትና የባሕል አጥር ውጭ መሆን አለበት፡፡ ብዝሃነትና አንድነት የማይቃረኑም የማይሸናነፉም መሆኑን በመገንዘብ መነሳት አለብን፡፡ አንድነት አንድ ዓይነትነት አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የተፈጥሮ ጌጥ የሆነውን ብዝሃነትን ደፍጥጦና ለንቅጦ ፍፁም አሃዳዊ ባሕል፣ ሕዝብና መንግሥት ማምረት ጥንትም ዛሬም ነገም አይሆንም፡፡ ተፈጥሯዊ ያልሆነ መሆኑንም ማስተዋል ያሻል፡፡

መሬት ያለውን እውነታ ተቀብሎ በብዝሃነትና በአንድነት መካከል ያሉትን የጋራና በጎ ጎኖች ማጎልበትና ለቁምነገር ማዋል ቀርቶ፣ አንዱ ሌላውን ማውገዝ፣ ማጥቃትና ማሳደድ ነገ በቀል ከመጋበዝ፣ ኅብረተሰብን ከማድማትና ከማፍረስ የማይዘል፣ የዛሬን ብቻ የሚመለከት የተሳሳተ ዕይታ ነው፡፡ አንዱን ወይም ሌላውን ብቻ ያለሚዛን መደገፍም ሆነ መንቀፍ ከነባራዊው ዓለም መጣላት ነው፡፡ በአንድ አገር የመኖር እውነታ እስካለ ድረስ፣ በሰላምና በመከባበር ለመኖር መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ የሕዝቦችን ተፈጥሮና መብት የማይደፈጥጥ፣ በፈቃድና በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሠረተ የጋራ ዓላማና ርዕይ የግድ ይላል፡፡

ሲራራ – Sirara