የሰላም አስከባሪዎቹ ተጠሪነታቸዉ ለተመድ በመሆኑ ድርጅቱ በሚያዘዉ መርህ መሰረት የሚወሰን ይሆናል – ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ከአብዬ አስወጭ ስለተባለችዉ የሰላም አስከባሪ ሀይል ምን አለች?

ኢትዮጵያ በአብዬ ያሏትን ሰላም አስከባሪያዎች የምታወጣዉ ሱዳን ስላለች ሳይሆን ከተመድ ጋር በመነጋገር ብቻ ነዉ ብላለች፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ኢትዮጵያ በአብዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ያሉትን ወታደሮች ያሰፈረችዉ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመነጋገር በመሆኑ፣ ወታደሮቹ ይዉጡ ቢባል እንኳ ሊወጡ የሚችሉት ሱዳን ስላለች ሳይሆን በድርጅቱ መርህ ነዉ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀዉ ሲመልሱ፣ የሰላም አስከባሪዎቹ ተጠሪነታቸዉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመሆኑ ድርጅቱ በሚያዘዉ መርህ መሰረት የሚወሰን ይሆናል ነዉ ሉት፡፡

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን መገንጠሏን ተከትሎ በድንበር አካባቢ ያለዉን ዉጥረት ለመረጋጋት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎችን ያሰፈረ ሲሆን የኢትዮጵያ ወታደሮችም እ.ኤ.አ ከ 2011 ጀምሮ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአብዬ ግዛት ከ4 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች የሚገኙ ሲሆን ባጠቃላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ያሉት ደግሞ 5 ሺህ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች በአብዬ ግዛት መኖርም በደቡብ ሱዳንና በሱዳን መካከል ያለዉን ዉጥረት ከማርገብ በተጨማሪ ቀጠናዉን ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ ሚና ያለዉ ተልዕኮ ነዉ ብለዋል አምባሳደሩ፡፡

ይሁን እንጂ ከህዳሴ ግድብ እና ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ዉዝግብ ጋር ተያይዞ፣ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰራዊት ከአብዬ ግዛት ይዉጣልኝ ማለቷ የሚታወስ ነዉ፡፡