ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያን ሀብታም አያደርጋትም (ክቡር ገና)

ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያን ሀብታም አያደርጋትም (ክቡር ገና)

ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) የበርካታ አገራትን ኢኮኖሚ በማንኮታኮት ይታወቃል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ራሺን፣ ግሪክን፣ ዩክሬንን፣ ጣሊያንንና አርጀንቲናን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ብድርን በተመለከተ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የብድር ገንዘብ ኢኮኖሚን ያሳድጋል የሚል ከእውነታው በእጅጉ የራቀና ለተረት ተረት የቀረበ የተሳሳተ መረጃ የሚመግብ አመለካከት ነው፡፡ ለዚህ አመለካከት አራማጆች ለተጨባጭ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆኑት የምርትና ፍጆታ ጉዳይ ድንታ አይሰጣቸውም፡፡ እነዚህ ወገኖች የብድር ገንዘብ አንድን አገር ወደ ማርና ወተት የሚፈስባት ምናባዊ አገር ያሸጋግራታል ብለው ይወተውታሉ፡፡ መንግሥታችን ከዚህ ወገን የሚመደብ ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ እምብዛም ድምጹ የማይሰማና እንዲሰማም የማይፈለግ አመለካከት ሲሆን ይህ ወገን ብድር በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበይናል ሲል ይሞግታል፡፡ በዚህም መሠረት ብድር አበዳሪውን አለቃ ተበዳሪውን ጭፍራ፣ አበዳሪውን ጌታ ተበዳሪውን ባሪያ ያደርጋል ሲሉ ይበይናሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋምና ዓለም ዐቀፍ የግል ባንኮች ከዓመታት በፊት በአርጀንቲና ኢኮኖሚ ያደረሰውን መንኮታኮትና በሕዝቡ ላይ ያስከተለውን መጎሳቆል መመልከት ብቻ በቂ ነው ባይ ናቸው፡፡

የአለም አቀፍ ብድርን በተመለከተ ተራው ሰው በየትም አገር ግራ እንደተጋባ ነው፡፡ ተራው ሰው (እሱ ወይም እሷ) በስተመጨረሻ ይህን የመንግሥት ብድር እንደሚከፍል አያውቅም፡፡ ለተራው ዜጋ ሕይወት ሁሌም ትግል ነች፡፡ ለለፍቶ አዳሪ ዜጎች ከገቢው በላይ የሚያወጣ ወንበዴና ሌባ ብቻ ነው፡፡ መንግሥታቸው ግን እየተበደረ ከገቢው በላይ ያወጣል፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት የ3 ቢሊዮን ዶላር ምርት ወደ ውጭ ልካ የ18 ቢሊዮን ዶላር ምትር ከውጭ ታስገባለች እንደሚባለው፡፡

እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ እስካሁን ባለው ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ ብድር በአራት እጥፍ አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ1999 የኢትዮጵያ የውጭ እዳ 7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አሁን ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል፡፡

ማንም ሰው በየትኛውም ሀገርና ወቅት ከገቢው በላይ እያጠፋ በዘላቂነት ሊኖር አይችልም፡፡ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አለ፡፡ ብድር በምንም መልኩ ካፒታል ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም የካፒታል ተቃራኒ ወይም ጸረ ካፒታል ነው፡፡ ብድር በአጭሩና በግልጽ ቋንቋ ሲገለጽ የነገን ገቢ ዛሬ በወለድ ተበድሮ መውሰድ ማለት ነው፡፡ ብድር አይደለም እንደተቆጠበ ገንዘብ ሊቆጠር ይቅርና እንደ ግኝት እንኳ ሊቆጠር አይችልም፡፡ በብድር የሚገኝ አንድ ዶላር በቁጠባ የተገኘውን አንድ ዶላር ይዞት ይሄዳል፡፡ ብድር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልገውን ቁጠባ እየሸረሸረው ይሄዳል፡፡

ብድርን የወቅቱ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ መሣሪያ አድርገው የሚሰቡ መሪዎች በበድር ጉዳይ የሚሰጥ ትችት እንደማይጥማቸው ይታወቃል፡፡ እኛም የውጭ ብድርን በተመለከተ የምንሰጠው ትችት የመሪዎቻችንን ጥረት ለማኮሰስ ሳይሆን ለአንባቢዎቻችን ሐሳባችንን ለማካፈል ነው፡፡ መቼም ሐሳባችንን ስናካፍል ሁሌ ትክክል መሆን አይጠበቅብንም ሐቀኛና ግልጽ መሆን እንጂ፡፡

እናም ርእሰ ጉዳያችን ወደ ሆነው ወደ ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም ስንመለስ ባለፈው ተቋሙ ለኢትዮጵያ እሰጣለው ስላለው የ3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጥቂት እንበል፡፡ ይህ ብድር ምን ያህል የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ያቃልላል? መሰረታዊ ችግሮችን ማቀለሉን ብንተው እንኳ የአጭር ጊዜ ቀውሶችን በማረጋገት መፍትሔ ይሰጠናል?

ብድሩ ኢትዮጵያ እዳዋን ለመክፈልና የብሔራዊ ባንክን የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግ ይረዳታል የሚለው የአንዳንድ ወገኖች ሐሳብ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ በርግጥ የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም ብድር በከፊል የአገሪቷን የውጭ እዳ ለመክፈል ቢያግዝም አገሪቱን ከእዳ ነጻ ለመሆን የሚያስችል ባለመሆኑ ይህን ያህል ተጋኖ የሚወራለት ተዓምር አይደለም፡፡

የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም ለአንድ አገር ገንዘብ ሲያበድር በቅድመ ሁኔታ ከታሰረ ውል ጋር ነው፡፡ ዝርዝሩ ይፋ ባይደረግም ኢትዮጵያም ከተቋሙ ገንዘብ ስታገኝ የምትገባቸው ግዴታዎች ይኖራሉ፡፡ በተለይም ብር ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ይወሰን ወይም የብር ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ ይቀንስ የሚሉ ግዴታዎች መቅረባቸው አይቀርም፡፡ እንዲህ ያሉ ግዴታዎች ደግሞ የገቢ ንግዷ ከወጪ ንግዷ በእጅጉ ለሚበልጥ ሀገር የሚያዋጣ አይደለም፡፡

ከዚያ በተረፈ ግን የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ እያለ የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ ያለ ተቋሙ መካሪነት እኛው ልናከናውነው እንችላለን፡፡ አብዛኞቹ ችግሮቻችን ምን እንደሆኑ እኮ አልጠፉንም፡፡ የውጭ አካል ካልጠቆመን አንስማም ካላልን በስተቀር ኢትዮጵያ በየሙያ መስኩ በርቃታ ሊኂቃን አሏት፡፡ ችግሩ ሰሚ ጆሮ መጥፋቱ ነው፡፡ የራስን ችግር በራስ ያለፍታት በራስ መተማመንን ክፉኛ ይጎዳል፡፡ ምክርን ከውጭ ብቻ የሚሰማ መንግሥት ደግሞ በዜጎቹ ዘንድ እምነትን ያጣል፡፡ እምነት ያጣ መንግሥት ደግሞ ምን እንደሚሆን በቅርቡ አይተናል፡፡

ሌላው እንደ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም ያሉ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችን መመሪያዎች ሁሉ እንደወረደ ተግባራዊ ማድረግ ፈተና የሚሆነው ለቀጣዩ መንግሥት ነው፡፡ ምንጊዜም ቀጣዩ መንግሥት በአመለካከትም ሆነ በአሠራር ስልቱ ካለፈው መንግሥት የመለየት ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ የቀድሞ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር የገባው ውል ለአዲሱ መንግሥት እንዲሁም ለህዝቡ እዳ ይሆናል፡፡

እናም በአጭሩ እቅጩን እንነጋገር ከተባለ ‘አይ. ኤም. ኤፍ’ የኢትዮጵያን ችግር በጭራሽ አይፈታም፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ እንዳየነውና እኛም በዕድሜያችን እንደምንመሰክረው ‘አይ. ኤም.ኤፍ’ እጁን ያስገባበት አገር አይደለም ሀብታም ሊሆን የነበረውም እንዳልነበረ ሲሆን ነው የታየው፡፡ የኒዮ ሊብራሊዝም አራማጅ የሆነው ይህ ተቋም የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች በዜጎች መካከል የለውን የኑሮ ልዩነት ይበልጥ የሚያሰፉ፣ ድህነት እንዲንሰራፋና ስር እንዲሰድ የሚያደርጉ፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ሀብት ወደ ግል በማዞር ስም ትርፍ በውጭ አገራት እንዲከማች የሚያርጉ ናቸው፡፡ እና ወገኖቼ ‘አይ. ኤም. ኤፍ’ አገራችንን ሀብታም ያደርጋታል ብላችሁ ታስባላችሁ?