ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደውዬ በመኪናው ውስጥ ተሳፋሪ የሆነችው ፍቅረኛው በጥይት ተመቷል ብላ መልስ ሰጠችኝ … ልጄ ህይወቱ አልፎ እዚያው ተጋድሞ ነበር

ቁጣን የቀሰቀሰው የ20 ዓመቱ ወጣት ግድያ :

ከሚኒያፖሊስ በስተሰሜን በምትገኘው የአሜሪካዋ ብሩክሊን ሴንተር ከተማ በትራፊክ ማቆሚያ ውስጥ ፖሊስ አንድን ጥቁር በጥይት መግደሉን ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች ተቀሰቀሱ።

ሰልፎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጪስ የተተኮሰ ሲሆን የሰዓት እላፊም ተጥሏል።

የግለሰቡ ዘመዶች ሟቹ የ20 ዓመቱ ወጣት እንደሆነ እና ዱዋንት ራይት እንደሚባል አስታውቀዋል፡፡

የብሩክሊን ሴንተር ከንቲባ ሰዎችን “ራሳችሁን ጠብቁ፣ ወደ ቤታቸው ሂዱ” በማለት የሰዓት እላፊ ጥለዋል።

ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል የተከሰሰ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን የፍርድ ሂደት እየተጀመረ መሆኑ በሚኒያፖሊስ ውጥረቱ ከፍተኛ ሆኗል፡፡

ከአሁኑ ረብሻ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ፍርድ ቤት ዛሬ ሥራ ይጀምራል። ዓቃቤ ሕግም ክሱን ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል፡

የሚኒሶታው ገዥ ቲም ዋልዝ “ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተልኩ ነው” ያሉ ሲሆን ለራይት ቤተሰቦች እየጸለዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቦታው የተፈጠረው ምንድን ነው?

እሑድ ዕለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የዱዋንት ራይትን ስም እየጠሩ በብሩክሊን ሴንተር ከሚገኘው የፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ውጭ ተሰባሰቡ፡፡

እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከሆነ ፖሊሶች አድማ መበተኛ መሳሪያዎችን ታጥቀው ሲወጡ፤ ውጥረቱ አይሎ ሁለት የፖሊስ ተሽከርካሪዎች በድንጋይ ተመተዋል፡፡

ሰልፈኞቹ በእግረኛ መንገዶች ላይ መልዕክቶችን ጽፈዋል፤ ሻማም አብርተዋል።

ፖሊስ ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ ያዘዘ ሲሆን የፖሊስ መኮንኖች አስለቃሽ ጭስና ድንገተኛ የእጅ ቦምቦችን ሲተኮሱ ታይተዋል፡፡

የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን በተወሰኑ አካባቢዎች ዝርፊያ እንደነበር ሲዘግቡ የብሩክሊን ሴንተር ከንቲባ ማይክ ኤሊዮት በትዊተር ገጻቸው የሰዓት እላፊ መጣሉን አስታውቀዋል፡፡

“ሁሉም ሰው ደህንነቱ መጠበቁን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። እባካችሁ ራሳችሁን ጠብቁ እና ወደ ቤትዎ ይሂዱ” ሲል ጽፈዋል፡፡

በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ምክንያት ክሱ የሚታየውን ዴሪክ ቻውቪን ችሎት እንዲጠብቁ የተሰማሩት የሚኒሶታ ብሔራዊ ዘቦችም ወደ ብሩክሊን ሴንተር ተልከዋል፡፡

የአከባቢው የመገናኛ ብዙሃን ብሩክሊን ሴንተር ሁሉንም ትምህርት ቤቶች እና ዝግጅቶች ለሰኞ ዘግቷል ብለዋል።

ዱዋንት ራይት ምን ሆነ?

የብሩክሊን ሴንተር ፖሊስ መምሪያ በሰጠው መግለጫ እንዳለው ፖሊሶች እሑድ ከሰዓት አንድን ሰው በትራፊክ ጥሰት ምክንያት ከመኪና ውስጥ የተቆጣጠሩት ሲሆን፤ በኋላም ቀደም ሲል የወጣበት የእስር ማዘዣ እንዳለው አወቁ፡፡

ፖሊስ ሊይዘው ሲሞክር እንደገና ወደ መኪናው እንደገባም ተናግረዋል፡፡

ከዚያ በኋላ አንድ የፖሊስ መኮንን አሽከርካሪው ላይ የተኮሰ ሲሆን ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ ከመቆሙ በፊት ብዙ ህንጻዎችን አልፎ ነበር፡፡ በቦታው ላይም ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡

በተሽከርካሪው ውስጥ የነበረች አንዲት ሴት ተሳፋሪ ደግሞ ለህይወቷ የማያሰጋ ጉዳት ደርሶባታል፡፡

በጉዳዩ የተሳተፉ መኮንኖች ልብሳቸው ላይ የተገጠሙ ካሜራዎችን ለብሰው እንደነበር ፖሊስ የገለጸ ሲሆን የመኪና ውስጥ ካሜራዎችም (ዳሽ ካሜራዎች) ይሠሩ እንደነበር ተነግሯል፡፡

የራይት እናት የሆኑት ኬቲ ትራፊክ ባስቆመው ወቅት ልጃቸው እንደደወለላቸው ገልጸው “የኋላ መመልከቻ መስታወቱ ላይ በተንጠለጠሉ የመኪና ጠረንን በሚያሳምሩ ተንጠልጣዮች” ምክንያት እንዲቆም መደረጉን ገልጾላቸው እንደነበርና በኋላም ጫጫታ እንደሰሙ እና የስልክ መስመሩ እንደተቋረጠ ተናግረዋል፡፡

“ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደውዬ በመኪናው ውስጥ ተሳፋሪ የሆነችው ፍቅረኛው በጥይት ተመቷል ብላ መልስ ሰጠችኝ … ልጄ ህይወቱ አልፎ እዚያው ተጋድሞ ነበር” ብለዋል።

የልጃቸው አስከሬን በፖሊሶች መሬት ላይ እንደተተወ ተናግረው “ማንም አንዳች ነገር አልነገረንም። ማንም አላነጋገረንም … እባካችሁ ልጄን ከመሬት ላይ አንሱ አልኩኝ” ማለታቸውን ስታር ትርብዩን ዘግቧል፡፡

ከንቲባ ኤሊዮት ተኩሱ “አሰቃቂ” መሆኑን ገልጸዋል። ገዥው ዋልዝ በበኩላቸው “ክልላችን በሕግ አስከባሪዎች ህይወቱ ለተቀጠፈ ሌላ ጥቁር ሰው ያዝናል” ብለዋል፡፡

በሚኒያፖሊስ ውጥረት ለምን ነገሰ?

በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ክስ የተመሠረተበት የዴሪክ ቻውቪን የፍርድ ሂደት በከተማዋ ላለፉት ሁለት ሳምንታት እየተካሄደ ነው፡፡

ባለፈው ግንቦት በሚኒያፖሊስ ቻውቪን የተባለው የፖሊስ መኮንን ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ለማዋል አንገቱ ላይ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በላይ ተንበርክኮ ተቀርጾ ነበር።

የክስተቱ ዘረኝነትን በመቃወም ዓለም አቀፍ ተቃውሞዎችን አቀጣጥሏል፡፡

ችሎቱ ቢያንስ አንድ ወር ይፈጃል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን ዳኛው የፍርድ ውሳኔ ላይ ከደረሱ በኋላ ሊመጣ ለሚችለው ብጥብጥ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ከወዲሁ እየተዘጋጁ ነበር።

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በከተማዋ ዙሪያ ተቃውሞዎችን ማስነሳቱ ይታወሳል። ተቃውሞዎቹ ብዙዎቹ ሠላማዊ ቢሆኑም አንዳንዶቹ በአመፅ የተሞሉ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎች የተጎዱበት ነበር፡፡

(BBC)