የብሔራዊ ባንክ የተሳከረ እርምጃ (ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር))


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የብሔራዊ ባንክ የተሳከረ እርምጃ (ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)) – ሲራራ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ከባንክ ውጪ ማስቀመጥ በሚቻለው የጥሬ የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት ለተቋማት 200 ሺሕ፣ ለግለሰብ 100 ሺሕ ብር ጣሪያ ተደርጎ በባንኩ ተወስኗል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ በገበያ ውስጥ ያለውን የጥሬ ገንዘብ መመጠን፣ በባንክ ቤት ያለውን የቁጠባ መጠን ማሻሻል እና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በዚህ ወቅት ምን ያህል ሰው ገንዘቡን በቤቱ ያስቀምጣል የሚለው በራሱ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በግሌ ከ10 እና 20 ሺሕ ብር በላይ በቤቱ የሚያስቀምጥ አለ ለማለት ይከብደኛል፡፡ መመሪያው በተለይ ኋላቀር በሆነው ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ከብት ለመግዛት ወደ ክፍለ አገር የሚሄድ ነጋዴ ጥሬ ገንዘብ መያዝ የምትችለው 100 ሺሕ ብር ነው ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከብቶቹን የሚገዛው ከተለያየ ቦታ እና በብዛት ነው፡፡ ማንም ሰው እንደሚረዳው አብዛኛው አርሶ አደር የባንክ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የባንክ ተደራሽነቱም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ መመሪያ በፊት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በባንኮች ላይ ተስፋ እና መተማመን እንዲኖረው የሚያስችል ሥራ መሠራት ነበረበት፡፡

ሰው በፈለገው ሰዓት ያለ ወረፋ እና ግፊያ ገንዘቡን ማንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ እና የባንክ ቴክኖሎጂ አስተማማኝ ከሆነ ማኅበረሰቡ ማንም ሰው ሳያስገድደው ገንዘቡን በባንክ ያስቀምጣል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሞባይል ባንኪንግ ለመጠቀም ያለው የኔትዎርክ ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደ ሆነ ለማንም የሚጠፋ አይደለም፡፡ ባንኮቻችን በአንድ የቴክኖሎጂ ሥርዓት እንኳን ሳይጣመሩ ይህን ዓይነቱን መመሪያ ማውጣቱ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ነው፡፡

የዚህ አገር መሠረታዊው ችግር የሥርዓት ነው፡፡ የባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ ስርዓት ያለው በባንኮቹ እጅ ሳይሆን በመንግሥት እጅ ነው፡፡ አብዛኛው የቴክኖሎጂ አቅም ዛሬም በመንግሥት እጅ ላይ ነው፡፡ ለባንኮች የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ደህንነት ጥበቃ የሚያደርገው መንግሥት ነው፡፡ መሠረተ ልማት አቅራቢውም መንግሥት ነው፡፡ በግልጽ እንደሚታየው መንግሥት ብቻውን ዘርፉን ማዘመን አልቻለም፡፡ መንግሥት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ማድረግ ያለበት በቁጥጥሩ ላይ መግዘፍ ሳይሆን ለዘርፉ የሚያስፈልገው መሠረተ ልማት ማሟላት ላይ ትኩረት ቢያደርግ ነው የሚሻለው፡፡

ቀደም ሲል የግል ባንኮች የተሻለ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ዛሬ ከመንግሥት ባንክ የሚሻል አገልግሎት መስጠት ተስኗቸዋል፡፡ ዛሬም አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቼክ ይዘህ ወጋገን አልያም ሌላ ባንክ ለመመንዘር ብትፈልግ ረጅም ቀናት ይፈጃል፡፡ በዚህ ያልዘመነ አሠራር ምክንያት አንድ ነጋዴ 20 የባንክ አካውንት እንዲከፍት እየተገደደ ነው ያለው፡፡ ብዙ የባንክ ሒሳብ ተከፈተ ማለት የባንክ ዘርፉ አደገ ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ እንዱ ሰው ነው አምስት እና ስድስት የባንክ ሒሳብ ደብተር የያዘው፡፡ እያንዳንዱ ባንክ እንደ አንድ ባንክ መናበብ ሳይችል ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ጣሪያ ለማውጣት መሯሯጡ አግባብ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች እርስ በርሳቸው መናበብ እንዲችሉ በቂ ድጋፍ ሳያደርግላቸው ቁጥጥር ላይ ብቻ ማዕከል አድርጎ መሥራቱ አግባብነት የለውም፡፡ ከመብራት አገልግሎት ጋር በተያያዘ፣ ከኔትዎርክ ግንባታ ጋር በተያያዘ ዛሬም ባንኮች ከመንግሥት ድጋፍን ይሻሉ፡፡ መብራት የለም ተብሎ በቅርንጫፎች ባንክ አገልግሎት የሚቋጥበት አገር ላይ ነው የለነው፡፡

ኤ.ቲ.ኤም ከመያዝ እና በስልኩ የሞባይል ባንኪንግ ከመጠቀም ይልቅ በኪሱ ጥሬ ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስን አማራጭ ያደረገ ማኅበረሰብ ነው ያለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ መሬት የወረደ ሥራ በመሠራት እንጂ ቢሮ ቁጭ ብሎ ሕግ በማርቀቅ መቀየር አንችልም፡፡

የመመሪያው ሌላው ምክንያት የዋጋ ንረትን ማረጋጋት የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ከጥሬ ገንዘብ አቅርቧት ጋር የሚገናኝ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ረገድ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ማውጣቱ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጋው ይችላል በሚለው ሐሳብም አልስማማም፡፡

አሁን በአገሪቱ የሚታየው የዋጋ ንረት እንደ ቀደመው ጊዜ በገበያ ውስጥ ባለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት የተፈጠረ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ምክንያት የምርት እጥረት ነው፡፡ የሚቀርበው ምርት እና ያለው ፍላጎት በፍፁም የሚጣጣም አልሆነም፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ በአቅርቦት ጎን (supply side) ችግር አለ፡፡ የዋጋ ንረቱ እየመነጨ ያለው በዚሁ በምርት አቅርቦት በኩል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የገንዘብ እንቅስቃሴው ላይ ገደብ ሲጣል የምርት አቅርቦቱ ላይ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ያሰጋል፡፡ ቢዝነስ እንቅስቃሴው በተዳከመበት ሁኔታ ባልሰለጠነ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ጥሬ ገንዘብ አታንቀሳቀስ ብሎ ማለት ቢዝነስ እንቅስቃሴን የባሰ መግደል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ሌላኛው ምክንያት በምርት ግብዓት ዋጋ ንረት የሚነሳ ነው፡፡ ከ60 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ የሚያመጡት ከውጪ አገር ነው፡፡ ለግብርናው ግብዓት የሚሆነው ማዳበሪያ የሚመጣው ከውጪ አገሮች ነው፡፡ ከቅርቡ ዓመታት ወዲህ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተመንን እያስወደደች በመሆኑ የግብዓቶቹ ዋጋ ጨምሯል፡፡ ያን ተከትሎ የምርቱ ዋጋ ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የዋጋ ንረትን የጥሬ ገንዘብ ገደብ በመጣል ገበያውን አረጋጋለሁ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን መሰል መመሪያ ከማውጣቱ አስቀድሞ ነጋዴው፣ አርሶ አደሩ፣ አልሚው፣ ደሞዝተኛው ወዘተ… ከባንክ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የሚለውን በአግባቡ በጥናት መመለስ ይገባዋል፡፡

ሲራራ – ቢዝነስ|ኢኮኖሚ!