መፍትሔ ያላገኘው የዋጋ ንረት – (ሁሴን አሊ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


መፍትሔ ያላገኘው የዋጋ ንረት (ሁሴን አሊ) –

ሲራራ – የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ካሳየበት ጊዜ አንስቶ ቁጥሩ ይለያይ እንጅ የዋጋ ንረት በተከታታይነት ሲከሰት ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ የዋጋ ንረት በከፍተኛ መጠን ከጨመረበት 1998 ዓ.ም. ወዲህ ሁለት ጊዜ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ አንደኛው በ1998 ዓ.ም. የተከሰተው ሲሆን፣ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ምጣኔ ነበረው፡፡ ለዋጋ ንረቱ በወቅቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የምግብ ምርት ዋጋ መናር ከፍተኛ አበርክቶ ነበረው፡፡ በአገር ውስጥ የነበረው የገንዘብ ልቀት ከፍተኛ መሆን ለዋጋ ንረቱ ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም. ላይ በተመሳሳይ ወደ 20 በመቶ የተጠጋ የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ የዋጋ ንረቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ማለፋቸውን ተከትሎ የተፈጠረ ነው፡፡ ከ8 ዓመታት በኋላ በ2013 ዓ.ም. ላይ የዋጋ ንረቱ ከ20 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡

አሁን ያለው የዋጋ ንረት በጣም አሳሳቢ እና እስካሁን ከነበረው ሁኔታም የተለየ ነው፡፡ የዋጋ ንረት እስከ 5 በመቶ ድረስ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚመከር እና ጤናማ የሚባል ነው፡፡ የንረት መጠኑ ከ10 በመቶ በላይ ከሆነ ጫና ያለው ሲሆን፣ ከ20 በመቶ እስከ 50 በመቶ የሚሆነው እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ የዋጋ ንረት ነው፡፡ አሁን በአገራችን የተከሰተው የንረት መጠን ከ20 በመቶ በላይ ስለሆነ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ ለዚህ ዋጋ ንረት መፈጠረ የተጠራቀሙ እና ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ በዛሬ መጣጥፍ እነዚህን ምክንያቶች ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

ከፍተኛ ገንዘብ ልቀት

ኢኮኖሚክስ ሳይንስ የዋጋ ንረትን ከጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ (ሞነተሪ ፖሊሲ) ጋር የሚገናኙት አሉ፡፡ በኢኮኖሚ ውስጥ ዘለግ ላሉ ዓመታት ከፍተኛ የገንዘብ ልቀት ካለ ልቀቱ የማኅበረሰብን ምርት የመጠቀም ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ምርት እያደገ ባለው የፍላጎት መጠን ልክ ማደግ ካልቻለ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡

በተለይ በታዳጊ አገሮች የሚከሰተው በዋጋ ንረት መሠረቱ የገንዘብ ልቀት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ታዳጊ አገሮች ኢኮኖሚውን ለማልማት በርካታ ገንዘብ ወደ ገበያው ይለቃሉ፡፡ ነገር ግን በገንዘብ ልቀቱ ምክንያት የሚፈጠረውን የምርት ፍላጎት የሚመጥን የምርት አቅርቦት የመፍጠር አቅም አይኖራቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ዐሥር ዓመታት መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ገበያው ሲለቅ እንደቆየ እና ይህም የዋጋ ንረቱን እንዳባባሰው መንግሥት አምኖ የተቀበለው ሐቅ ነው፡፡

የዳበረ የገበያ ሥርዓት አለመኖር

አብዛኛቹ ታዳጊ አገሮች በዕዝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የቆዩ ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች አሁን ወደ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ሲገቡ ቀድሞ የተደራጀ እና የተጠናከረ የገበያ ሥርዓት የሌላቸው በመሆኑ ገበያቸው የተረበሸ ይሆናል፡፡ ገበያቸው በመንግሥት ሲመራ የቆዩ አገሮች የብዙሃኑ የገበያ ሥርዓታቸው ደካማ ነው፡፡ ይህን ደካማ የገበያ አስተዳደር ሥርዓት ይዘው ወደ ነጻ ገበያ ሲገቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲፈጠር ይስተዋላል፡፡ ለአብነት በኢትዮጵያ ያለው የገበያ ሥርዓት የአቅርቦትም ሆነ የምርት ፍላጎት ጎን ምክንያት ለሚፈጠረው የዋጋ ንረት ምላሽ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚክ ሳይንስ መሠረት የምርት ዋጋ ሲጨምር የምርት መጠንም ተያይዞ ይጨምራል፡፡ የምርት ዋጋ መጨመር አምራቹ ተጨማሪ ምርት እንዲያመርት ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ግን የምርት ዋጋ ቢጨምርም የምርት መጠን አብሮ ሲጨምር አናይም፡፡ ይህ የሚያሳየው ገበያው ምን ያህል የተረበሸ መሆኑን ነው፡፡ በገበያው ላይ በሚታየው የዋጋ ጭማሪ ተጠቃሚ የሚሆነው አምራቹ ሳይሆን ደላላው እና ነጋዴው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ገበያው የተረበሸ ለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ ገበያው ላይ ‹ሞኖፖሊ› እና ‹ኦሊጎፖሊ› ሥርዓት መኖሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ ብዙ አምራች ቢኖርም ምርት አከፋፋዩ ግን ጥቂት ነው፡፡ መሠረታዊ ምርቶችን ከውጭ የሚያስገቡት ምርት አስገቢዎችም ጥቂት ናቸው፡፡ አንዳንድ ዘርፎች በጥቂት ሰዎች እጅ ላይ ናቸው፡፡ በገበያው ሰንሰለት ላይ ያሉ ተዋንያን እና ደላሎች በርካታ መሆናቸው ገበያው ጫና እንዲፈጥሩ አድርገዋል፡፡ እነዚህ አካላት በምርት ላይ ዕሴት ሳይጨምሩ ለገበያው ዋጋ ሰጪ እና ተማኝ መሆናቸው ለዋጋ ንረቱ መባባስ ቀልፍ ሚና እንዲጫወቱ አድርጓል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት እና የካፒታል አቅም መዳከም
በኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ምርት ማመረት እንዲችል የሚያደርግ ኢንቨስትመንትን ለመትከል የሚያስችል በቂ የካፒታል አቅም የለም፡፡ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ትልቁን ብድር የሚወስደው መንግሥት ነው፡፡ ከብድር ባለፈ በዚህ አገር ከፍተኛው ኢንቨስትመንትም የመንግሥት ነው፡፡

በሌላ በኩል የባንኮች የትርፍ ኅዳግ በጣም ኋላቀር ከመሆኑ ባለፈ አሳታፊነቱም ዝቅተኛ ነው፡፡ የአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ጥሬ ገንዘብን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ምክንያት ባንኮች በቂ የብድር አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ በባንክ ገንዘቡን የሚያስቀምጠው እና የሚቆጥበው 10 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ነው፡፡ ባንኮች ባላቸው አቅም ውስንንነት ምክንያት በግልም ይሁን በቡድን ብድር ለሚፈልጉ አካላት በቂ ብድር እየሰጡ አይደለም፡፡ ይህም በአገሪቱ ጠንካራ ኢንቨስትመንት እንዳይኖር አድርጓል፡፡

የሕዝብ ቁጥር መጨመር

በታዳጊ አገሮች ከፍተኛ የውልደት መጠን አለ፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ 25 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ አሁን 110 ሚሊዮን አልፏል፡፡ የአገሪቱ የምርት ዕድገት ግን በዚህ ልክ አላደገም፡፡ የሚፈጠረው አዲስ የሰው ኀይል የሰለጠነ እና አምራች ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ክፍተት አለ፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ አምራች መሆን ካልቻለ የሚጨምረው የፍላጎት መጠንን ነው፡፡ ይህ እያደገ ያለ የሕዝብ ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ አምራች የማይሆን ከሆነ የምርት እጥረት መግጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ እየገጠመም ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚተዳደረው በግብርና ዘርፍ ነው፡፡ ከፍተኛ የውልደት መጠንም ያለውም በዚህ በገጠሩ የአገራችን ክፍል ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በገጠር ያለው ማኅበረሰብ አቅሙን የሚገነባበት ሁኔታዎች አልተፈጠረም፡፡ ወደ ከተሞች አካባቢ በቀን ሥራ ለመሰማራት ከገጠሩ ወደ ከተማ እየፈለሰ ያለው የገጠሩ ወጣት ነው፡፡ ወጣቶች ባሉበት እየተደገፉ ምርት እንዲጨምር የሚያደርግበት ሁኔታ ቢፈጠር የምርት አቅምን በመጨመር ፍላጎትን ማርካት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ይህ ሲተገበር አልቆየም፡፡

የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ችግር

የኢንዱስትሪ ፖሊሲያችን የውጭ ንግድን መሠረት ያደረገ መሆኑ የዚህ አገር ምርት አቅርቦት ዕድገት እንዳይኖረው አንዱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ወደ ውጭ ከሚላከው ምርታችን እስካለፈው ስድስት ወር ድረስ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የግብር ምርት ነው፡፡ ከዚያ ተከትሎ ያለው ማዕድን ነው፡፡ በርካታ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቶ፣ ያ ሁሉ የአስፓልት መንገድ ተሠርቶ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከውጭ ንግዳችን ያለው ድርሻ 15 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ጥቅሙ ከግብርና የተሻለ አይደለም፡፡

የውጭ ንግድን የሚያበረታታ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ውጤት ያላመጣ ፖሊሲ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች ቀድሞ ከውጭ የሚመጣውን ምርት መተካት ላይ ትኩረት ማድረግ ቢችሉ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአገር ውስጥ ያለውን የምርት እጥረት መፍታት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተደራረቡ መምጣታቸው አሁን ለተፈጠረው የዋጋ ንረት ታሪካዊ ምክንያቶች እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል ኢንቨስትመንት የሚፋፋበትን ዕድል ማመቻቸት ይገባል፡፡ ለዚህም የፋይናንስ ተቋማት አቅም መጠናከር ዋናው ተግባር ነው፡፡

የገበያ ሥርዓቱ የሰለጠነ መሆን እንዲችል በገበያ ውስጥ ያሉትን ሕገ-ወጥ ተዋንያን ማጥራት፤ ምርት ከአምራች ወደ ተጠቃሚ በቀላሉ መድረስ እንዲችል የገበያ ሂደቱን ጥራት ባለው ሥርዓት መመራት ያስፈልጋል፡፡ የአርሶ አደሩ ልጅ እዛው ባለበት የንግድ ሥራ ፈጣሪ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ የሥራ ፈጠራ እና ከኢንቨስትመንት ጋር ያሉ ቢሮክራሲ የሞላባቸው አሠራሮች መጥራት እና የተቀላጠፈ አገልግሎቶች የሚሰጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ቢሮክራሲ የሞላበት አሠራር መፍትሔ ሲያገኝ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፡፡ ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ ምርት ያድጋል፡፡ ምርት ሲያድግ ደግሞ የገበያ ዋጋ ይረጋጋል፡፡

ሲራራ-ቢዝነስ|ኢኮኖሚ!