ለኢትዮጵያ የለውጥ ጅማሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እየሰጠው ነው

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ሪፎርም ሂደት እውቅና እየሰጠው ነው- መንግስት

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን ሪፎርም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እየሰጠው መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡፡

ጽ/ቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫው በነሃሴ ወር ብቻ የእንግሊዝ፤ የጀርመን፤ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፤ የቪዬትናም፤ የሳኡዲ ዓረቢያ እና ሌሎች በርካታ ሃገራት ከፍተኛ ልኡካን ቡድን ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡

ይህም ሃገሪቱ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዘርፍ እያካሄደች ላለው ሪፎርም እውቅና እና ድጋፍ መስጠታቸውን የሚያሳይ ነው ብሏል ጽ/ቤቱ፡፡

በንግድ፤ ግብርና፤ ኢንቨስትመንት፤ አቅም ግንባታ፤ ትምህርት እና በሌሎች መስኮችም ከሃገራቱ ጋር ተባብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱ ለውጡ በዲፕሎማሲ በኩልም ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን እንደሚያሳይ ነው የገለጸው፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት መካከልም በተደረጉት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የግጭት ስጋቱ መሰረታዊ በሚባል ደረጃ መቀነሱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያስታወቀው፡፡

ይህ ሁሉ ድል ሊመዘገብ የቻለው በኢትዮጵያዊያን መካከል የነበረው የጥላቻ ግንብ በመፈራረሱና የአንድነት፤ የፍቅር እና የመተባበር ስሜት በህዝቡ ዘንድ በመስረጹ ነው ብሏል፡፡

በመሆኑም የተጀመረውን የይቅርታ፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የመደመር ጉዞን አጠናክሮ ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡

ይህን ጉዞ ለማደናቀፍ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተደረጉ ያሉ ድርጊቶችን ማስቆም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሃላፊነት ሊከታተለው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡